ውሉደ ብርሀን ሰ/ት/ቤ/ት🙏(ጫንጮ)
766 subscribers
84 photos
4 files
98 links
ሰንበት ትምህርት ቤት የመልካም ወጣት የመልካም ትውልድ መፍለቂያ ናት! ትውልድን ለበጎ ነገር የምታበቃ ናት፡፡


የጫንጮ ከተማ ደ/ብ/ቅ/እግዚአብሔር አብ እና ደ/ሲ/ቅ/ ኪዳነ ምህረት ቤ/ክ ው/ብ/ሰ/ት/ቤት ቻናል
ለሀሳብ እና አስታየት @weldebirhanbot @ty1921 ይጠቀሙ

ወንድሞች በህብረት ቢቀመጡ መልካም ነው፡፡
Download Telegram
.💚💛❤️💚💛❤️💚💛❤️💚💛❤️💚💛❤️

#ኪዳነ ምህረት

ኪዳነ ምህረት ማለት የምህረት መሐላ ማለት ነው፡፡

ከ33ቱ በዓላተ እግዝእትነ ድንግል ማርያም አንዱ ነው፡፡ እመቤታችንም ከጌታችን መቃብር እየሄደች በምትለምንበት ጊዜ አይሁድ ለምቀኝነት አያርፉምና ምን ልታመጣብን ነው በማለት ሊጣሏት ሲመጡ ጌታችንም ከዓይናቸው ሰውሯታል አይሁድም ጠባቂ ቢያቆሙ እመቤታችን ዕለት ዕለት መሄዷን አላቋረጠችን እመቤታችንም እንዲህ ብላ ስትጸልይ ልጄ ወዳጄ ሆይ ከስጋዬ ስጋ ከነፍሴ ነፍስ ነስተህ ሰው በመሆንህ ዘጠኝ ወር ከ5 ቀን በቻለችህ ማሕጸኔ ከአንተ ጋር ሀገር ለሀገር ስለ መሰደዴ መጥተህ ልምናዬን ትሰማኝ ዘንድ እለምንሃለሁ አለች በዚህ ጊዜ ንውጽውጽውታ ሆነ መቃብራት ተሰነጣጠቀ ጌታችንም እልፍ ከእልፍ መላዕክቱ ጋር መጥቶ ሰላም ለኪ ማርያም ምን እንዳደርግልሽ ትለሚኚኛለሽ አላት፡፡

እርሷም መታሰቢያዬን ያደረገውን ስለ ስሜ ለችግረኛ የሚራራውን በስሜ ቤተ ክርስቲያን ያነጻውን መባዕ የሰጠውን ከሃይማኖት ከፍቅር ጽናት ልጁን በስሜ የጠራውን ሁሉ ማርልኝ ከሞተ ስጋ ከሞተ ነፍስ አድንልኝ አለችው፡፡

ጌታችንም ይህን ሁለ እንዳደርግልሽ በራሴ በአባቴና በመንፈስ ቅዱስ ስም ቀል እገባልሻለው ብሎ ቃል ገብቶላት አርጓል።

በዚህም የተነሳ እመቤታችን እኛን በምልጃዋ የምታስምርበተ ፣ ጥያቄያችንን የምታስመልስበት ፣ እንቆቅልሻችንን የምታስፈታበት የምህረት ኪዳን የካቲት 16 ተቀብላለች እና ኪዳነ ምህረት እንላታለን ።


💚💛❤️💚💛❤️💚💛❤️💚💛❤️💚💛https://t.me/yeberhanljoche
💠 #ኢየሱስ_ክርስቶስ የሕያው የእግዚአብሔር ልጅ ነው። 💠

✧ በወንጌልም ሆነ በተለያዩ የሀዲስ ኪዳን የመልእክት ክፍሎች ውስጥ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅ እንደሆነ ተጠቅሶ ይገኛል። እንደውም ማንኛውም ክርስቲያን፥ ኢየሱስ እግዚአብሔር ልጅ መሆኑን ማመን መቀበል እንዳለበት አጽንኦት ተሰጥቷል፡፡

✧ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በቂሳርያ ሀዋርያቱን ሰብስቦ ሰዎች ማን እንደሚሉት በጠየቃቸው ጊዜ አንዳንዶች ኤልያስ ከነብያት አንዱ እንደሆነ እንደሚናገሩ ሲነግሩት እናንተ ማን እንደሆንኩ ትላላችሁ ብሎ ቢጠይቃቸው ክርስቶስ የህያው እግዚአብሔር ልጅ እንደሆነ ቅዱስ ጴጥሮስ ተናግሯል ጌታችንም ቅዱስ ጴጥሮስን አመስግኖ ስጋና ደም እንዳልገለጠለት የሰማዩ አባቱ እንደገለጠለት በመናገር በዚህ በቅዱስ ጴጥሮስ ንግግር ቤተክርስቲያኑን እንደሚመሰርት ጌታ ተናግሯል ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅ ነው የሚለው የቅዱስ ጴጥሮስ ንግግር የቤተክርስቲያን መሰረት ነው። የጌታን ማንነት የሚገልጽ እምነታችን መሰረት ነው፡፡

✧ ኢየሱስ የእግዚአብሔር ልጅ እንደሆነ የማያምን እንዲሁም ብሎ የማይመሰክር ሰው ክርስቲያን ተብሎ ሊጠራ አይችልም ምክንያቱም የክርስትና መሰረት ይህ ስለሆነ ‹‹ኢየሱስም ወደ ፊልጶስ ቂሣርያ አገር በደረሰ ጊዜ ደቀ መዛሙርቱን። ሰዎች የሰውን ልጅ ማን እንደ ሆነ ይሉታል? ብሎ ጠየቀ። እርሱም፦ አንዳንዱ #መጥምቁ_ዮሐንስ ፥ ሌሎችም #ኤልያስ ፥ ሌሎችም #ኤርምያስ ወይም #ከነቢያት_አንዱ ነው ይላሉ አሉት።
እርሱም፦ #እናንተስ #እኔን ማን እንደ ሆንሁ ትላላችሁ? አላቸው።
ስምዖን ጴጥሮስም መልሶ፦ #አንተ #ክርስቶስ_የሕያው_እግዚአብሔር_ልጅ ነህ አለ። ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አለው፦ የዮና ልጅ ስምዖን ሆይ፥ #በሰማያት ያለው #አባቴ እንጂ #ሥጋና #ደም ይህን #አልገለጠልህምና #ብፁዕ ነህ። እኔም እልሃለሁ፥ አንተ ጴጥሮስ ነህ፥ በዚችም ዓለት ላይ ቤተ ክርስቲያኔን እሠራለሁ፥ የገሃነም ደጆችም አይችሉአትም። የመንግሥተ ሰማያትንም መክፈቻዎች እሰጥሃለሁ፤ በምድር የምታስረው ሁሉ በሰማያት የታሰረ ይሆናል፥ በምድርም የምትፈታው ሁሉ በሰማያት የተፈታ ይሆናል።››ማቴ 16፡13-19

ቅዱስ ገብርኤልም እመቤታችንን ለማብሰር በተላከ ጊዜ ከእርሷ የሚወለደው <<ቅዱሱ የእግዚአብሔር ልጅ>> እንደሚባል ነግሯታል እሷም ይህንን በእምነት ተቀብላ ስግው ቃል/ሰው የሆነ አምላክ/ እግዚአብሄርን በስጋ ወልዳዋለች ስለዚህም ወላዲተ አምላክ ብለን እንጠራታለን፡፡ የሉቃስ ወንጌል 1፡35 ‹‹መልአኩም መልሶ እንዲህ አላት፦ መንፈስ ቅዱስ በአንቺ ላይ ይመጣል፥ የልዑልም ኃይል ይጸልልሻል ስለዚህ ደግሞ ከአንቺ የሚወለደው ቅዱስ የእግዚአብሔር ልጅ ይባላል።››

✧ በተለያየም ቦታ አጋንንት እኳን ሳይቀሩ የእግዚአብሔር ልጅ እንደሆነ መስክረዋል፡፡ ማቴ 8፡29 አይሁድም የእምነታችን መሰረት የሆነውን የእግዚአብሔር ልጅነቱን አልተቀበሉም ነበር፡፡ማቴ 26፡63 ይዘብቱበትም ነበር ማቴ 27፡43 ፡፡ ቅዱስ ማርቆስም ወንጌሉን ሲጀምር እግዚአብሔር ልጅነቱን መስክሮ ነው ማር1፡1፡፡ በተለያየ የቅዱስ ዮሐንስ ወንጌል ክፍል ውስጥ ኢየሱስ የእግዚአብሔር ልጅ መሆኑ ተጠቅሷል ይህንንም እናመን ዘንድ ወንጌል እንደተፃፈ ይነግረናል ዮሐ 1፡34 ፤1፡50 ፤6፡69 ፤ 10፡36 ፤11፡4 ፤11፡27 ፤ 19፡7 ፤ 20፡31፡፡

✧ ኢትዮጵያዊው ጃንደረባ ይህንን አምኖ እንደተጠመቀ መጽሐፍ ቅዱስ ይነግረናል ሐዋ 8፡37፡፡ቅዱስ ዮሐንስ በመልእክቱም ኢሱስ የእግዚአብሄር ልጅ እንደሆነ ተናግሯል ‹‹ ኢየሱስ የእግዚአብሔር ልጅ እንደ ሆነ በሚታመን ሁሉ እግዚአብሔር በእርሱ ይኖራል እርሱም በእግዚአብሔር ይኖራል።››1ኛ የዮሐንስ መልእክት 4፡15፡፡

እንግዲህ ከላይ እንደተመለከትነው መጽሀፍቅዱስ አፅንኦት ሰጥቶ ኢየሱስ የእግዚአብሔር ልጅ እንደሆነ በእግዚአብሔር ልጅነቱም ማመን እንዳለብን ይናገራል...

??? ለመሆኑ ኢየሱስ የእግዚአብሔር ልጅ ሲባል ምን ማለት ነው ???

✧ ኢየሱስ የእግዚአብሔር ልጅ ነው ሲባል መፅሐፍ ቅዱስ እንደሚነግረን እግዚአብሔር ነው ማለት ነው። እኛ የሰው ልጆች ሰዎች እንደምንባል ሁሉ የእግዚአብሔር ልጅ የሆነው ኢየሱስም እግዚአብሔር ተብሎ ይጠራል፡፡ ኢየሱስ እግዚአብሔር ነው ሲባል አብን በመልክ የሚመስለው በባህሪ የሚስተካከለው ማለታችን ነው ዮሐ 1፡1-3 ፤ ዮሐ 10 ፡30 ፤ዮሐ 14፡8-10 ‹‹እኔና አብ አንድ ነን እኔን ያየ አብን አይቷል››፡፡ ልጅነቱም የባህሪ ልጅነት ነው ማለትም ከማንም ያልተቀበለው ማንም የማይወስድበት ዘላለማዊ ልጅነት ነው፡፡

✧ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የአብ ልጅ እንደሆነ ከአብ ጋር አንድ እንደሆነ እና አብ የሚያደርገውን ሁሉ እንደሚያደርግ ለአይሁድ ሲነግራቸው ድንጋይ አንስተው ሊወግሩት በማሰባቸው ጌታችን ስለምን ትወግሩኛላቻሁ ባላቸው ጊዜ ስለመልካም ስራህ አንወግርህም ስለስድብህ ነው ሰው ስትሆን ራስህን አምላክ ስለማድረግህ ነው ማለታቸው በወንጌል ተመዝግቧል እንግዲህ አይሁድ ኢየሱስ የእግዚአብሔር ልጅ ነኝ ማለቱ አምላክ ነኝ ማለቱ እንደሆነ ገብቷቸዋል ማለት ነው ዮሐ 10፡25-38

✧ ከዚህ ጥቅስ እንደምንረዳው ጌታችን ራሱን የእግዚአብሔር ልጅ ብሎ መጥራቱ አምላክ ነኝ ማለቱ እንደሆነ ነው/ ሙሉውን የአይሁድ እና የጌታን ንግግር አንብቡት/፡፡በሌላም ቦታ አይሁድ የእግዚአብሔር ልጅ ነኝ ብሎ ራሱን መጥራቱን ተቃውመው ሊገሉት እንደነበር የእግዚአብሄር ልጅ ነኝ ማለቱ ደግሞ እግዚአብሔር ነኝ ማለቱ እንደሆነ ተረድተውት ሊገሉት እንደሚፈልጉ ተገልጧል ‹‹እንግዲህ ሰንበትን ስለ ሻረ ብቻ አይደለም፥ ነገር ግን ደግሞ ራሱን ከእግዚአብሔር ጋር አስተካክሎ <<
እግዚአብሔር አባቴ ነው ስላለ፥ ስለዚህ አይሁድ ሊገድሉት አብዝተው ይፈልጉት ነበር።››ዮሐ 5፡18

✧ ስናጠቃልለው ኢየሱስ እግዚአብሔር ልጅ ተብሎ መጠራቱ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ እንደተመለከትነው አምላክ/እግዚአብሔር መሆኑን የሚገልጥልን ልጅነቱም ከማንም ያልተቀበለው ባህሪ ልጅነት እንደሆነ እግዚአብሄርንም የሚስተካከልበት ልጅነት በመልክ ሚመስልበት ልጅነት እንደሆነ ልንረዳ ያስፈልጋል፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር
🇪🇹🇪🇹🇪🇹🇪🇹🇪🇹🇪🇹🇪🇹🇪🇹🇪🇹🇪🇹🇪🇹🇪🇹
ሰላም የተዋህዶ እምነት ተከታዮች በሙሉ🙏

ከዛሬ ጀምሮ በአዲሱ ቻናላችን ስለ ሰ/ት/ቤቱ መረጃዎች እንዲሁም ስለተዋህዶ ሀይማኖት እየፃፍን እናቀርባለን።
ጎደኛዎትን ለመጋበዝ ከፈለጉ ከታች የለዉን ሰማያዊ ሊንክ ሼር በማድረግ አባልነቶን ያሳዩን።

@yeberhanljoche @yeberhanljoche
@yeberhanljoche @yeberhanljoche
ስማኝ ልጄ!!!!!!!

1. ጠንካራ ሰው ሁን ማለት አትውደቅ ማለት አይደለም ወድቀህ መነሳትንም ልመድ ማለት እንጂ!!!!

2. ዝም በል ማለት አትናገር ማለት አይደለም ሌሎችን ለመስማት ጆሮ ስጥ ማለት እንጂ!!!!

3. ሆዳም አትሁን ማለት አትብላ ማለት አይደለም በሰው ሀቅ አትለፍ ማለት እንጂ!!!!

4. አትቆጣ ማለት ስሜት አይኑርህ ማለት አይደለም ከቁጣ ቶሎ ተመለስ ማለት እንጂ!!!!

5. ይቅርታ አድርግ ማለት አልተጎዳህም ማለት አይደለም በሆድህ ቂም መያዝ ሌላ ጉዳት ስለሆነ እንጂ!!!!

6. ጠላትህን ውደድ ማለት ጠላት ጥሩ ነው ማለት አይደለም ከጥላቻ ይልቅ ፍቅር ስለሚያሸንፍ!!!

7. ደስተኛ ሁን ማለት ሁሉ ይኑርህ ማለት አይደለም ባለህ ነገር ደስ ይበልህ ማለት እንጂ!!!!

8. ስራህን ውደድ ማለት የምትሰራው ስራ ጥሩ ነው ማለት አይደለም ነገ ጥሩ ስራ እንዲኖርህ ዛሬ የምትሰራውን ስራ ውደድ ማለት እንጂ!!!!

9. ወረኛ አትሁን ማለት አታውራ ማለት አይደለም ምንም ስለማታውቀው ነገር አታውራ ማለት እንጂ!!!!

10. ትሞታለህ ማለት አትስራ ማለት አይደለም ምንም ቁም ነገር ስትሰራ አትሙት ማለት እንጂ!!!!

11. ብቸኛ አትሁን ማለት ሮጠህ ትዳር ያዝ ማለት አይደለም ልብህን ግዜህን ያለህን ሁሉ አሳልፈ ለመስጠት ዝግጁ ሁን ማለት እንጂ!!!!

12. እውነተኛ ሁን ማለት ሰዎች ባሉበት ብቻ እውነትተናገር ማለት አይደለም ለራስህም የእውነት ኑሮ ኑር ማለት ማለት እንጂ!!!!

13. አትጣላ ማለት ከሰው ጋር አትኑር ማለት አይደለም ቂም ይዘህ አትቆይ ማለት እንጂ!!!!

14. ኩራተኛ አትሁን ማለት አትዘንጥ ማለት አይደለም ሌሎችን አትናቅ ማለት እንጂ!!!

15. ቆንጆ ነህ ማለት ከሌሎች የተሻልክህ ነህ ማለት አይደለም አምሮብሃል ማለት እንጂ!!!!

16. አዋቂ ሁን ማለት እንደገና ት/ቤት ሂድ ማለት አይደለም ብልህ ሁን ማለት እንጂ!!!!

@yeberhanljoche
@yeberhanljoche
@yeberhanljoche
እንኩዋን ለሊቀ መላእክት "ቅዱስ ሚካኤል" እና "ለቅዱሳኑ" ዓመታዊ በዓል በሰላም አደረሳችሁ

ቅዱስ ሚካኤል ሊቀ መላእክት

=>ቅዱስ ሚካኤል በጥንተ ተፈጥሮ በኢዮር: ኃይላት በተባሉት ነገደ መላእክት ተሹሞ ነበር:: ሳጥናኤል በካደ ጊዜ እግዚአብሔር ባወቀ: አንድም በትሕትናውና ደግነቱ በ99ኙ ነገደ መላእክት ላይ ሁሉ ተሹሟል::

+ከፍጥረት ወገን ከእመቤታችን ቀጥሎ የቅዱስ ሚካኤልን ያሕል ክብርና ርሕሩሕ የለም:: በምልጃውም: በረዳትነቱም የታወቀ መልአክ ነው:: መጽሐፍ "መልአከ ምክሩ ለእግዚአብሔር" ይለዋል:: "ወስሙ መስተሣሕልም" ይለዋል:: ቂም የሌለው: ለምሕረት የሚፋጠን: ደግ መልአክ ነውና::

+በብሉይ ኪዳን በመከራ ለነበሩ ቅዱሳን ሁሉ ሞገስ: ረዳትና አዳኝ ቢሆናቸው "መጋቤ ብሉይ" ተሰኝቷል:: እሥራኤልን 40 ዘመን በበርሃ መርቷል:: መግቧልም:: ቅዱስ መጽሐፍ ስለ እርሱ ብዙ ይላል:: (ዘፍ. 48:16, ኢያ. 5:13, መሳ. 13:17, ዳን. 10:21, 12:1, መዝ. 33:7, ራዕይ. 12:7)

+ደስ የሚለው ደግሞ ርሕሩሑ መልአክ ከእመቤታችን ጋር ልዩ ፍቅር አለው:: ከእናቷ ማሕጸን ጀምሮ እስከ ዛሬ እነሆ አብሯት አለ:: ደስ ብሎት ይታዘዛታል:: ማማለድ ሲፈልግም "እመቤቴ ሆይ! ቅደሚ" ይላታል:: ወደ እሳት መጋረጃ አብረው ገብተው ለዓለም ምሕረትን: በረከትን ያወርዳሉ::

+"+ ቅዱስ ኢያሱ ነቢይ +"+

=>ዳግመኛ በዚህች ዕለት ቅዱስ ሚካኤል ኢያሱን እንደ ረዳው ታስተምራለች:: ይህስ እንደ ምን ነው ቢሉ:-

+በመጽሐፈ ኢያሱ ምዕራፍ 5 ላይ እንደ ተጻፈው ቅዱሱ መልአክ ለኢያሱ ተገልጦለታል:: እሥራኤልን በምድረ በዳ የመራ ሊቀ ነቢያት ቅዱስ ሙሴ ሲያርፍ ታላቅ ሐዘንና ድንጋጤ ተፈጥሮ ነበር::

+እግዚአብሔር ግን ኢያሱን አስነስቶ አረጋግቷቸዋል:: ቅዱስ ሚካኤል 40ውን ዘመን እሥራኤልን ደመና ጋርዶ: መና አውርዶ: ክንፉን ዘርግቶ: ጠላትን መክቶ ከሙሴ ጋ እንደ መራቸው ከኢያሱ ጋርም ይሆን ዘንድ ከሰማይ ወረደ::

+በኢያሪኮ አካባቢም የተመዘዘ ሰይፉን ይዞ በግርማ ለኢያሱ ታየው:: ኢያሱም ወደ እርሱ ቀርቦ "አንተ ከእኛ ወገን ነህን? ወይስ ከጠላቶቻችን?" ሲል ጠየቀው:: ቅዱስ ሚካኤልም መልሶ "እረዳህ ዘንድ እነሆ የሠራዊት አለቃ ሆኜ ተሹሜ መጥተቻለሁ" አለው::

+ያን ጊዜ ታላቁ ነቢይ ቅዱስ ኢያሱ በግንባሩ ተደፍቶ ለሊቀ መላእክት ቅዱስ ሚካኤል ሰገደለት:: ቅዱሱ መልአክም አክሎ "ፍታሕ ቶታነ አሳዕኒከ እም እገሪከ: እስመ ምድር እንተ ትከይዳ ቅድስት ይዕቲ - የረገጥካት ምድር የተቀደሰች ናትና ጫማህን ከእግርህ አውጣ" አለው::

+ኢያሱም የተባለውን አደረገ:: ለዚህ ነው ቤተ ክርስቲያናችን "ለመላእክት የጸጋ (የአክብሮ) ስግደት ይገባል: በቅዱሳኑ ፊትም ጫማ ተለብሶ አይቆምም" የምትለው:: ያ መሬት ሊቀ መላእክት ቢቆምበት ተቀድሷል:: ዛሬም ቤቱ በታነጸበት: ታቦቱ በተቀረጸበት ቦታ ሁሉ ቅዱሱ መልአክ አለና ጫማን አውልቆ: ባጭሩ ታጥቆ መግባት ይገባል::

+ሊቀ መላእክት ቅዱስ ሚካኤል ከኢያሱ ጋር ሆኖ አማሌቅን ጨምሮ የእሥራኤልን ጠላት አጥፍቷል:: ጥቅመ ኢያሪኮን (ቅጥሩን) አፍርሷል:: ምድረ ርስትን አውርሷል:: በገባኦን ፀሐይን: በቆላተ ኤሎምም ጨረቃን ሲያቆም ከእርሱ ጋር ሆኖ ረድቶታል::

+"+ ዱራታኦስና ቴዎብስታ +"+

=>ቅዱሳኑ ዱራታኦስ (ዶርታኦስ) እና ቴዎብስታ (ቴዎብስትያ) የቅዱስ ሚካኤል ወዳጆች ናቸውና በዚህች ዕለት ይታሰባሉ:: በድርሳነ ሚካኤልና በመጽሐፈ ስንክሳር ተጽፎ እንደምናገኘው 2ቱ ቅዱሳን በተቀደሰ ትዳር ተወስነው: ሕጉን ትዕዛዙን ፈጽመው: ለነዳያን ራርተው: ቅዱስ ሥጋውንና ክቡር ደሙን ተቀብለው የሚኖሩ ነበሩ::

+ይልቁኑ ግን የጌታችን: የእመቤታችንን እና የቅዱስ ሚካኤልን መታሰቢያ ያለማስታጐል ያደርጉ ነበር:: ከጊዜ በሁዋላ ግን ሐብት ንብረታቸው አልቆ ተቸገሩ:: ግን የጨነቃቸው መቸገራቸው ሳይሆን የቅዱስ ሚካኤልን መታሰቢያ ሊያቆሙ መሆናቸው ነው::

+አማራጭ ሲያጡ ተቀምጠው ተመካከሩ:: የቅዱሱ መልአክ ዝክር ከሚቀር ልብሳቸውን (ያውም የክብር ልብሳቸውን) ሊሸጡ ተስማሙ:: በዚህ መሰረት ቅዱስ ዱራታኦስ ወደ ገበያ ሲሔድ ወዳጁ ቅዱስ ሚካኤል ከሰማይ ወረደለት::

+መንገድ ላይም የጦር መኮንን ሃገረ ገዢ መስሎ ተገናኝቶ አጫወተው:: ችግሩን ጠይቆም መፍትሔውን ነገረው:: "እኔ እዋስሃለሁና ለበዓል የሚያስፈልጉህን ነገሮች ሁሉ ገዝተህ አሰናዳ" አለው::

+"እኔ ወደ ቤትህ መጥቼ ስለምስተናገድ አንድ አሣ አምጥተህ አቆየኝ:: እኔ ሳልመጣ ግን አትረደው" አለው:: ቅዱስ ዱራታኦስ የተባለውን ሁሉ ፈጽሞ ወደ ቤቱ ሲሔድ ድንቅ ነገርን ተመለከተ:: ሚስቱ ቅድስት ቴዎብስታ በቤቱ መካከል ሁና ቤቱ በበረከት ሞልቷል::

+ማሩ: ቅቤው: እሕሉ ሁሉ በየሥፍራው ሞልቷል:: ባልና ሚስቱ ደስ ብሏቸው:: ነዳያንን ሲያበሉ: እንግዳ ሲቀበሉ ዋሉ:: በሁዋላ ያ መኮንን (ቅዱስ ሚካኤል) በቤታቸው መጥቶ ተስተናገደ::

+በእርሱ ትዕዛዝ የአሣው ራስ (ሆድ) ሲከፈት በውስጡ 300 ዲናር ወርቅ (እንቁ) ተገኘ:: ቅዱሳኑ ይህን ተመልክተው ሲደነግጡ ቅዱስ ሚካኤል ክንፉን ዘርግቶ ራሱን ገለጸላቸው:: ደንግጠው በግንባራቸው ተደፉ::

+እርሱ ግን "በተገኘው ሃብት እዳችሁን ክፈሉ:: ከዚህ በሁዋላ ግን በምድር አትቸገሩም:: በሰማይም ክፍላችሁ ከእኔ ጋር ነው" ብሎ ባርኩዋቸው ወደ ሰማይ ዐረገ:: እነርሱም በሐሴትና በበጐ ምግባር ኖረው ዐርፈዋል:: ለርስቱም በቅተዋል::

+"+ ቅዱስ ባሕራን ቀሲስ +"+

=>የደጋግ ክርስቲያኖች ግን የድሆች ልጅ::
*በሕጻንነቱ በግፍ ወደ ባሕር የተጣለ::
*በእግዚአብሔር ጥበብ አድጎ የግፈኛውን ንብረት የወረሰ::
*በመልካም ትዳር በቅስና ያገለገለ::
*ምጽዋትን ያዘወተረ::
*አብያተ ክርስቲያናትን ያሳነጸ ደግ ክርስቲያን ነው::
¤አርፎ ቅዱስ ሚካኤል ወዳጁ በዕረፍተ ገነት አኑሮታል::

+"+ አፄ በእደ ማርያም +"+

=>"በዕደ ማርያም" ማለት "በማርያም እጅ" እንደ ማለት ነው:: እኒህ ሰው የኢትዮዽያ ንጉሥ ሲሆኑ የነገሡትም በ1460 ዓ/ም ነው:: ደጉ አባታቸው አፄ ዘርዓ ያዕቆብ ሲያርፉ በመንግስቱ ተተክተው ሃገራችንን አስተዳድረዋል:: ድርሰት ደርሰዋል:: አብያተ መቃድስ አንጸዋል::

+በተለይ ለቅኔ ትምሕርት ማበብ ልዩ የሆነ አስተዋጽኦ እንዳደረጉ ይነገራል:: ልክ በነገሡ በ10 ዓመታቸው ግን መንግስተ ምድር በቃኝ ብለው በምናኔ በርሃ ገብተዋል:: በዙፋናቸውም አፄ እስክንድር ተተክተዋል:: ጻድቁ ንጉሥ ግን ቅዱስ ሚካኤልን ይወዱት ነበርና በዚህች ቀን ዐርፈዋል::

=>አምላከ ቅዱሳን በክንፈ ሚካኤል ከክፉው ሁሉ ይሰውረን:: ከበረከታቸውም አይለየን::

=>ኅዳር 12 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት=
1.ቅዱስ ሚካኤል ሊቀ መላእክት
2.ቅዱስ ኢያሱ ነቢይ
3.ቅዱሳን ዱራታኦስና ቴዎብስታ
4.አፄ በዕደ ማርያም ጻድቅ
5.ቅዱስ ዮሐንስ መጥምቅ
6.ቅዱስ ባሕራን ቀሲስ
7.አባ ፊላታዎስ ሊቀ ዻዻሳት
@yeberhanljoche
ንነኳን ለሊቀ መላኩ ቅዱስ ሚካኤል አመታዊ ክብረ በአል አደረሳችሁ አደረሰን🙏🙏🙏
አንድ እለት አንድ ወጣት
አንድን የበቁ አባት
በማለት ጠየቀ በጣም ፈልጋለሁ አምላኬን ለማየት
ከልብህ ከፈለክ አምላክን ለማግኘት
ልምራህ ወዳለበት ተነስ ተከተለኝ
ታዲያ ግን አደራ ልመለስ አትበለኝ
አምላክን ለማየት ከልብህ ከፈለግክ
እርሱ ወዳለበት ስንሄድ ታየዋለክ
ካሉት በኋላማ ተነሱ በአንድነት ወደ አምላክ ሊሄዱ
ከጠበቀው በላይ ሩቅ ሲሆንበት ወጣቱ መንገዱ
እስኬት ነዉ ምንሄደው አምላክ የት ነው ያለው
እርሱ አምላክ ሳለ በዚህ በበረሃ ለምን ነው ሚኖረው
እኔ ግን አባቴ ልሞት ነው ደክሞኛል
ከምነግሮት በላይ ጉሮሮዬ ደርቋል
አባቴ ይንገሩኝ አምላክ የት ይገኛል
እኔስ ሄድኩ እንበል እርሱ ግን ያውቀኛል
አሁን ተቃርበናል ልንደርስ ነው አምላክ ጋ
እዚሁ ጠብቀኝ እኔ ግን ልሄድ ነው ሚጠጣ ፍለጋ
አሉትና እኚያ አባት ፈጥነው ተራመዱ
ወጣቱም በድካም ተንጋሎ አያቸው በፍጥነት ሲሄዱ
እራሱን ጠየቀ እጅጉን ተገርሞ
እኚህ አባት ጥንካሬያቸውን ኬት አመጡት ደግሞ
እኚያ አባት ሄደው ትንሽ እንደቆዩ
ወጣቱ ዞረበት ምድርና ሰማዩ
አምላኬን ሳላየው ልሞት ይሆን እንዴ
ምነው ግን ቢያቆየኝ እስካገኘው አንዴ
ብሎ ሳይጨርሰው እዚያው ራሱን ሳተ ተንጋሎ ሜዳ ላይ
ልክ እንደ ነቃ ዙሪያ ገባውን ሲያይ
እኚያ አባት ተቀምጠው ይፀልዩ ነበር
እሱም ቀና ብሎ የሚፀልዩትን ይሰማቸው ጀመር
ይስሙኝማ አባቴ
አምላኬን አየሁት ለዚያውም ሁለቴ
ወዴት አገኘኸው እንዴትስ ለየኸው
ባገኘኸው ጊዜስ ምንድን ነበር ያልከው
እኔ ወጣት ሆኜ በድካም ስሰቃይ
እርሶ ግን ሸምግለው ጥንካሬዎትን ሳይ
ያን ጊዜ አየሁት አምላኬን በእርሶ ላይ
ውሃ ጠምቶኝ ደክሞኝ ህሊናዬን ስቼ
ስነቃ ለየሁት ፀሎቶን ሰምቼ
በል አድምጠኝ ልጄ ታዲያ አሁንስ ገባህ
አምላክ ሁሌም አለ በዙሪያ በደጅህ
ይገለፅልህ ዘንድ
የትም ሳትሰደድ
በተስፋ ጠብቀው ልቦናህን ከፍተህ
ይህንን ስትፈፅም ያኔ ታየዋለህ

@yeberhanljoche
🌿🌾#በዓታ_ለማርያም🌾🌿

እመቤታችን አባትና እናቷ ኢያቄምና ሐና በስዕለት (ለቤተ መቅደስ ሊሰጡ ብፅዓት ገብተው) ያገኟት ናት፡፡ በአባት በእናቷ ቤትም ፫ ዓመት ተቀመጠች፤ ከእንግዲህ ወዲያማ ስእለት መብለት ይሆንብን የለምን ወስደን እንስጥ ብለው ይዘዋት ወደ ቤተ መቅደስ ሲሄዱ ዘካርያስም ሕዝቡን ሰብስቦ ጉባኤ አድርጎ ቆያቸው።
ከዚያውም ደርሰው እነሆ ተቀበሉን አሏቸው እነርሱም እንቀበላለን ብለው ቢያዩዋት ከፀሐይ ፯ እጅ አብርታ፥ ከመብረቅ ፯ እጅ አስፈርታ፥ ዕንቈ ባሕርይ መስላ ታየቻቸው፤ እነርሱም እኛ ይህችን የመሰለች ፍጡር ምን እናደርጋታለን? ምን እናበላታለን? ምን እንጋርድላታለን? ብለው ሲጨነቁ በዚህም መካከል እመቤታችንን እግዝእትነ ማርያም መንፈሳዊ ረኀብ ተነስቶባት ምርር ብላ አለቀሰች።
ያን ጊዜ መልአኩ ፋኑኤል በመሶበ ወርቅ ኅብስት ሰማያዊ፤ በብርሃን ጽዋዕ ስቴ ሕይወት ይዞ ረቦ ታያቸው፡፡ ሕዝቡም ዘካርያስን አባታችን ይህ የወረደው ክብር ላንተ ነው የሚኾነውና ተነስተህ ታጥቀህ እጅ ነስተህ ሰግደህ ተቀበል አሉት፤ ዘካርያስም እሽ ብሎ እጅ ነስቶ ሰግዶ እቀበላለሁ ብሎ ሲጠጋ ወደ ሰማይ ራቀው፥ መጠቀው፡፡ ከሕዝቡም እያንዳንዱ እየተነሱ እንቀበላለን ብለው ቢያዩ ወደ ሰማይ ራቃቸው፥መጠቃቸው፡፡
ከዚህም በኋላ ዘካርያስ ሐናን ጠርቶ ለናንተ ለእንግዶች የወረደ ክብር እንደሆነ ሕፃኒቱን ይዘሽ ወደዚያ ፈቅ ብለሽ ተቀመጪ አላት፡፡ እርሷም ሕፃኒቱን ይዛ ወደዚያ ፈቅ ብላ ተቀመጠች፡፡ መልአኩም ከራሳቸው ላይ ረቦ አልወርድም አለ፡፡
ሁለተኛም ዘካርያስ ሐናን ጠርቶ አምላከ እስራኤል የሚያደርገውን ነገር የሚያውቅ የለም፤ ሕፃኒቱን ከዚያው ትተሽ አንቺ ወዲህ ነዪ አላት፤ እሽ ብላ ሕፃኒቱን እዚያው ትታ ወደነሱ ሄደች፡፡ ያን ጊዜ መልአኩ ፋኑኤል ወርዶ ፩ ክንፉን ጋርዶ ፩ ክንፉን አጎናፅፎ ኅብስቱን አብልቷት፥ ወይኑን አጠጥቷት፤ እመቤቴ ሆይ መንገድ ባስመታሁሽ ማሪኝ ብሎ የብርሃን መሶብ፥ የብርሃን ጽዋ ይዞ ወደ ሰማይ ዐረገ፡፡
ሕዝቡም የምግቧማ ነገር ከተያዘ ከሰው ጋራ ምን ያጋፋታል፤ ቦታዋ ከቤተ መቅደስ ይሁን እንጂ ብለው ዙፋኑን ዘርግተው፥ ምንጣፏን አንጥፈው፥ መጋረጃውን ግራና ቀኝ ጋርደው ከቤተ መቅደስ አኖሯት፡፡
ይኸውም የተደረገው ታኅሣሥ ፫ ዕለት ነው፤ በኣታ የሚለው ስያሜም የተሰጠው በዚሁ ነው፡፡ ‹‹አመ ፫ ለታኅሣሥ በኣታ›› እንዳለ መቅድመ ተአምር፡፡ በዚህም፤
መቅደሲቱ ወደ መቅደስ ገባች፤
ቅድስቲቱ ወደ ቅድስት ገባች፤
ክብርቲቱ ወደ ክብርት ቤቷ ገባች፤
ልዩ የሆነችው ወደ ልዩ ሥፍራ ገባች፤
ቅድስተ ቅዱሳኗ ወደ ቅድስተ ቅዱሳን ገባች፤
ንጽሕተ ንጹሐኗ ወደ ንጽሕ አዳራሽ ገባች፤
ቤተ መቅደሷ ወደ ቤተ መቅደስ ገባች፡፡
ሊቃውንትም ‹‹መቅደስ ዘኢትትነሠት /የማትፈርሺ መቅደስ ነሽ››/ እያሉ አመሠገኗት፡፡
እመቤታችን እግዝእትነ ማርያም ኅብስት ሰማያዊ እየተመገበች፤ ስቴ ሕይወት እየጠጣች ከመላእክት ጋራ እየተጫወተች 12 ዓመት በቤተ መቅደስ ተቀመጠች፡፡
‹‹ከመዝ ነበርኪ ውስተ ቤተ መቅደስ፤ ወመላእክት ያመጽኡ ወትረ ሲሳየኪ ከመዝ ነበርኪ ፲ተ ወ፪ተ ዓመተ እንዘ ትትናዘዚ እምኀበ መላእክት ወስቴኪኒ ስቴ ሕይወት ውእቱ። ወመብልዕኪኒ ኅብስት ሰማያዊ››። እንዳለ ሊቁ ቅዱስ ያሬድ
ምግቧ ከየት የተገኘ ነው ቢሉ በገበሬ እጅ ያልተዘራ በቤተ ሰብእ እጅ ያልተሠራ በእግዚአብሔር እጅ የተፈጠረ ያማረ የተመረጠ ነው እንጂ ፡፡ ‹‹ኦ ድንግል አኮ ኅብስተ ምድራዌ ዘተሴሰይኪ፤ አላ ኅብስተ ሰማያዌ እም ሰማየ ሰማያት ዘበሰለ፡፡ ኦ ድንግል አኮ ስቴ ምድራዌ ዘሰተይኪ አላ ስቴ ሰማያዌ እምሰማየ ሰማያት ዘተቀድ›› (ድንንግል ሆይ ምድራዊ ኅብስትን የተመገብሽ አይደለሽም፤ ከሰማየ ሰማያት የበሰለ ሰማያዊ ኅብስትን እንጂ፡፡ ድንግል ሆይ ምድራዊ መጠጥን የጠጣሽ አይደለሽም፤ ከሰማየ ሰማያት የተቀዳ ሰማያዊ መጥን ነው እንጂ፡፡) /እንዳለ ሊቁ አባ ሕርያቆስ/።
✞ ስታድግም በንጽሕናና በቅድስና ነው፡፡ ‹‹ድንግል ሆይ አንገታቸውን እንደሚያገዝፉ እንደ ዕብራውያን ሴቶች ልጆች በዋዛ ያደግሽ አይደለም በንጽሕና በቅድስና ኖርሽ እንጂ።›› /እንዳለ ሊቁ አባ ሕርያቆስ/
✞ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በቤተ መቅደስ ሳለች አይሁድ ብዙ የክፋት ምክር ይመክሩ ነበር። ከዚህም ውስጥ አንዱ መጥቁል ወደሚባል ጠንቋይ ሄደው ‹‹ፍታሕ ማዕከሌነ ኢያቄም ወሐና›› ብለው እመቤታችንን እንዲያጠፋ እጅ መንሻን ሰጡት፤ መጥቁልም በመካከል አይሁድ በኋላ ሁነው ነጋሪት እየጎሰሙ፥ እምቢልታ እየነፉ እመቤታችንን እግዝእትነ ማርያምን ለመግደል ለቤተ መቅደስ ፪ ምንዳፈ ሐፅ ሲቀራቸው፤ ዓለም ከተፈጠረ ጀምሮ እስከ እዚያ ድረስ ያልተደረገና ያልተነገረ መብረቅ ነጎድጓድ ወርዶ አጋንንትንም፥ መጥቁልንም፥ አይሁድንም ቀጥቅጦ አጠፋቸው። እመቤታችን እግዝእትነ ማርያም በማግሥቱ ወጥታ አይታ መጥቁል ሆይ እኔን አጠፋ ብለህ መጥተህ አንተ እንዲህ ሆንህ ካንተ መከራ መዓት ያወጣኝ አምላክ ይክበር ይመስገን ብላ ፈጣሪዋን አመሰገነች፡፡ ከዚህ በኋላ በድኑ ለዝክረ ነገር የ፫ ቀን መንገድ እየሄደ ይሸት ጀመር።
✞እመቤታችን እግዝእትነ ማርያም ‹‹ዮሰሜር፣ አድሜሽ፣ ድቸር፣ አዶናዊሮስ፣ ሰራሰቅሰሬል›› ብላ የአምላክ ኅቡዕ ስምን ብትደግም መሬት ተከፍቶ ዋጣቸው ከነሥጋቸውም ሲኦል ወረዱ፡፡ ከዚህ በኋላ እመቤታችን እግዝእትነ ማርያም እጅግ ታፈረች የሚናገራት ጠፋ ‹‹ኦ ግርምት ድንግል›› /እንዳለ ሊቁ ቅዱስ ኤፍሬም/።

🙏የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያም ጣዕጧ፡ ፍቅሯ፡ በረከቷና ረድኤቷ ከልጅዋ ከወዳጅዋ ከመድኃኒታችን ከፈጣሪያችንና ከአምላካችን ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር ለዘላለሙ ይኑር፡፡ አሜን🙏
@yeberhanljoche
ታህሳስ 6 ቅድስት አርሴማ አፅሟ የፈለሰበትና ቅዳሴ ቤቷ የከበረበት ዓመታዊ ክብረ በዓሏ ነው ።
#ሰማዕቷ_ቅድስት_አርሴማ
በዚች ቀን ቅድስት አርሴማ ቤተክርስቲያኗ የከበረበትና የስጋዋ ፍልሰት የሆነበት እለት ነው
እናታችን ቅድስት አርሴማ እግዚአብሔርን በቅንነት ያገለግሉ ከነበሩ ከከበሩ ካህናት ወገን ከሆኑ ከቅዱስ ቴዎድሮስና ከእናቷ ቅድስት አትናሲያ በስዕለት ተወለደች፡፡ ሰማዕቷ ቅድስት አርሴማ ብሉይን ሐዲስን ተምራ እያነበበች እንዲሁም በተግባር እየተረጎመች ዘወትርም በጸሎት ትተጋ እንደነበር ገድሏ ይተርካል፡፡ በዚህ ዘመን ድርጣድስ የሚባል በአርመን የነገሠ አረማዊ ንጉሥ ለጣዖት የሚሰግድ' ፀሐይንም የሚያመልክ' ክርስቲያኖችንም እኔ ለማመልከው አምላክ መስገድ አለባችሁ በማለት መከራ ያጸናባቸው ነበር፡፡
እናታችን ቅድስት አርሴማም ተጋድሎዋን የጀመረችው የዚህ ጨካኝ ንጉሥ አገልጋይ ወይም ሹም ፳፯ ክርስቲያኖችን እንደልማዱ እየደበደበ' እየገረፈና ልዩ ልዩ ስቃይ እያደረሰባቸው ሲወስዳቸው በማየቷ ነበር፡፡ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ‘‘ለእነርሱና ለአሕዛብ ምስክር እንዲሆን ስለኔ ወደገዢዎችና ወደ ነገሥታት ትወሰዳላችሁ፡፡’’ (ማቴ. ፲፡፲፮፡፲፱)፡፡ ያለውን በማሰብ ቅድስት አርሴማም ገና በሃያ ዓመቷ የዚህን ዓለም ንጉሥ እኩይ ግብሩን በመንቀፍ ስለ ክርስቶስ ከሚሰቃዩ ወገኖቿ ጋር ግንባር ቀደም በመሆን ትመሰክር ጀመር፡፡ የንጉሡም አገልጋይ በደም ግባቷና በንግግሯ ማማር ተደንቆ በዚች በፈቃዷ ልትሠዋ በወደደች ሴት ምንም ሊያደርግባት ስላልወደደ ወደ ንጉሡ ወደ ድርጣድስ ከሃያ ሰባቱ ክርስቲያኖች ጋር ወሰዳት፡፡ ንጉሡም ብዙ የተነገረላትን ወጣት ሲያይ በውበቷና በንግግሯ ተማርኮ ለዓለማዊ ደስታውና ፍላጎቱ ተመኛት፡፡ ለእርሱም ሙሽራ እንድትሆን ብዙ ወተወታት፡፡ ቅድስት አርሴማ ግን ናቀችው ‘‘እኔ የሰማያዊው ንጉሥ የክርስቶስ ሙሽራ እንጂ የዚህን ዓለም አላፊ ጠፊ የሆነውን ገንዘብና ደስታ የምሻ አይደለሁም፡፡’’ በማለትም መለሰችለት፡፡ ንጉሡም ይህንን ከእርሷ በመስማቱ እጅግ ተቆጣ፤ በመናቁም ተበሳጨ፤ አሽከሮቹንም ጠርቶ በቤተ መንግሥቱ የታሰሩትን አንበሶች እንዲለቀቅባቸው አዘዘ፡፡ አንበሶቹ ግን ይደሰቱ ነበር፡፡ በኋላም ፊታቸውን ወደ ንጉሡና አገልጋዮቹ በማዞር ሩጠው እስኪደበቁ ድረስ አሳደዷቸው፡፡ ንጉሡ ይበልጥ ነደደው ክርስቲያኖቹ በረሃብ እንዲያልቁ እንዲታሰሩ አዘዘ፡፡ እግዚአብሔርም በአምስተኛው ቀን በብርሃን ቤቱን ሞልቶት የሚበሉትን በመሶብ የሚጠጡትን በጽዋ ከሰማይ አወረደላቸው፡፡ ንጉሡም ይህንን በማየቱ ከዚያ አውጥቶ በእሳት ውስጥም አስገባቸው፡፡ ሠለስቱ ደቂቅን የጠበቀ አምላክ እነርሱንም አዳናቸው፡፡ በሌላም በብዙ መንገድ ሊያጠፋቸው እንደሞከረ ገድሏ ይተርካል፡፡ በመጨረሻም ከአማካሪዎቹ ጋር ተማክሮ በሰይፍ እንዲያልቁ ይወስናሉ፡፡ እያንዳንዳቸውን ተራ በተራ ሲሰይፋቸው ቅድስት አርሴማ ለሚሰየፉት ሁሉ የድል አክሊል ከሰማይ ሲወርድላቸው ትመለከት ስለነበር የእርሷን ተራ በጉጉት ትጠብቀው ነበር፡፡ በመደሰቷም እየጸለየች አይዟችሁ ጽኑ ትላቸው ነበር፡፡ በመጨረሻም ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ጽናቷን ተመልክቶ ቃል ኪዳን ይገባላታል፡፡ ንጉሡም ሌሎቹን አሰይፎ ሲያበቃ ወደሷ ዞሮ በቁጣ እየጮኸ አንቺን እንደ ባልንጀሮችሽ በቀላሉ አልገልሽም ስቃይሽን አጸናብሻለሁ ብሎ ለአገልጋዮቹ ትእዛዝ በመስጠት አይኗን አስወጥቶ በእጇ ያሲዛታል፤ ጡቷን ያስቆርጣል፤ በኋላም አንገቷን ያሰይፋታል በዚሁ ሁኔታ እናታችን ሰማዕትነትን ተቀበለች፡፡
ይህንን ሁሉ መከራ ስለአምላኳ ስትል እራሷን አሳልፋ የሰጠች ድንቅ ሰማዕት ናት፡፡
@yeberhanljoche
#ከክርስቶስ_በፊት_የነበሩ_ክርስቲያኖች
(ዲያቆን ሄኖክ ኃይሌ)

#የቆሎ_ተማሪዎች

ንጉሥ ናቡከደነፆር እስራኤልን ድል ነሥቶ በግዞት ወደ ባቢሎን በወሰዳቸው ጊዜ ሕዝቡን ለአመጽ እንዳያነሣሡበት ከነገሥታትና መሳፍንት ወገን የሆኑትን ፣ መልከ መልካሞቹን ፣ ወጣቶቹንና ብሩሕ አእምሮ ያላቸውን መርጦ ከሕዝቡ ለይቶ በቤተ መንግሥቱ ሰበሰበ፡፡ ዓላማው ወጣቶቹ የሀገሩን ቋንቋ ከተማሩና በቤተ መንግሥት በምቾት ከኖሩ የወገኖቻቸው መከራ እንደማይሰማቸው በማሰብ ነበር፡፡ ከሰው ልጅ የሚበዛው እርሱ እስከተመቸውና ጥቅሙ እስካልተነካበት ድረስ የሌላው ወገኑ ጩኸት ስለማይሰማው ናቡከደነፆር እስራኤልን ለማፈን የተጠቀመው አደገኛ ስልት ነበረ፡፡ ይህ ስልት ግን በሦስቱ ወጣቶች በአናንያ በአዛርያና ሚሳኤል ላይ አልሠራም፡፡ ገና ከጅምሩ በቤተ መንግሥት የቀረበላቸውን ‹ጮማና ጠጅ አንበላም ጥሬ ይሠጠን› ብለው በድብቅ ‹የቆሎ ተማሪዎች› ሆኑ፡፡
መቼም የቤተ መንግሥትን እንጀራ አንዴ አትልመደው እንጂ የለመድከው እንደሆነ ንጉሡ ምንም አድርግ ቢልህ ታደርጋለህ፡፡ የቤተ መንግሥት ምግብ መዘዙ ብዙ ነው፡፡ ‹‹ኦርዮም ከንጉሡ ቤት ሲወጣ ማለፊያ እንጀራ ተከትሎት ሄደ›› ተብሎ እንደተጻፈ እንኳን የናቡከደነፆር ቤተ መንግሥት ምግብ ይቅርና የንጉሥ ዳዊት  ቤተ መንግሥት ምግብም እንደ ኦርዮ ሞትን ሊያስከትልም ይችላል፡፡ ከቤተ መንግሥት የሚሠጥህን ምግብ አገኘሁ ብለህ ደስ ቢልህም ያ ምግብ የመጨረሻ ራትህ ሊሆን ይችላል ወይም ደግሞ ነገ ክፉ ነገር አድርግ ቢሉህ እምቢ ለማለት ትቸገራለህ፡፡ ስለዚህ ሦስቱ ወጣቶች ጥሬ ቆርጥመው ሊማሩ ወሰኑ፡፡ ከዚህ በኋላ ነው ሦስቱን ወጣቶች ከንጉሡ ጋር የሚያጋፍጥ ነገር የመጣው፡፡

ከዚህ በኋላ ናቡከደነፆር ሕልም አለመ ፤ ሆኖም ሕልሙ ጠፋበት፡፡ አስማተኞቹን ሰብስቦ ‹ሕልሜን ከነፍቺው ንገሩኝ› ብሎ አፋጠጣቸው፡፡ ግራ ገባቸው ፤ ሕልሙን ተናግሮ ቢሆን ‹ሲሳይ ነው ፣ ዕድሜ ነው  ፣ ጸጋ ነው› ብሎ ማለፍ ይቻል ነበር፡፡ አሁን ግን ‹ሕልሜን ውለዱ› አለ፡፡ አልነግር ሲሉት ሊገድላቸው ወሰነ፡፡ በዚህ መካከል ሦስቱ ወጣቶች ከአጎታቸው ዳንኤል ጋር ሆነው መፍትሔ አመጡ፡፡ እነርሱ በጸሎት ሲተጉ እግዚአብሔር ሕልሙን ከነትርጓሜው ለዳንኤል ገለጠለት፡፡
ንጉሡ በዘነጋው ሕልሙ ያየው ‹ራሱ የወርቅ ፣ የቀረው አካሉ የብር ፣ የናስ ፣ የብረትና ሸክላ የሆነ ትልቅ ምስል ነበር› ዳንኤል ሕልሙን ለንጉሡ ከነገረው በኋላ እንዲህ ብሎ ፈታለት፡፡ ‹ንጉሥ ሆይ ባየኸው ሕልም ላይ በሥልጣን ከሁሉ በላይ አድርጎሃልና የወርቁ ራስ አንተ ነህ ፤ ከዚያ በታች ያየኻቸው ደግሞ ከአንተ በኃይል የሚያንሡ ከአንተ በኋላ የሚነሡ ነገሥታት ናቸው›› ብሎ እርሱና ከእርሱ በኋላ የሚነሡ ነገሥታት እንዴት መንግሥታቸው እንደሚያልፍ ሕልሙን ከነዝርዝር ፍቺው ነገረው፡፡ በዚህም ንጉሡ ደስ አለውና ዳንኤልን ከፍ ከፍ አደረገው ፤ ሦስቱን ወጣቶችም በአውራጃ ሥራ ላይ አዛዦች አድርጎ ሾማቸው፡፡

#እንደ_ንጉሡ_አጎንብሱ

ናቡከደነፆር ዳንኤል ከፈታለት ረዥም ሕልም ውስጥ ግን ከአእምሮው ያልጠፋችው ‹ወርቁ አንተ ነህ› የምትለው ዓረፍተ ነገር ነበረች፡፡ መቼም እኛ ወርቅ የሆንንበት ቅኔ ከልባችን አይጠፋም፡፡  ስለዚህ ራስ ወዳዱ ናቡከደነፆር ከረዥሙ ሕልም ውስጥ ‹ወርቁ አንተ ነህ› የምትለዋ ብቻ ልቡን ነካችው፡፡ ባልንጀራህን ‹እንደ ራስህ ውደድ› ስለሚል ራስን መውደድ ጥፋት አይደለም፡፡ ራስን መውደድ በጣም ከፍ እያለ ሲመጣ ግን ‹ፀሐይ የምትወጣው እኔን ለማየት ነው› እስከማለት ያስደርሳል፡፡ ናቡከደነፆር በራሱ ፍቅር ወደቀ ፣ ራሱን አቅፎ ለመሳም ቃጣው ፤ በመጨረሻም ‹እኔ ወርቅ ነኝ› የምትለው አሳቡ አድጋ በዱራ ሜዳ ላይ ትልቅ የወርቅ ሐውልት ሆነች፡፡ ‹ለዚህ ጣዖት የማይሰግድ ሰው ወደ እሳት ይጣላል› የሚል አዋጅ አወጀ፡፡ የመለከትና የእንቢልታ የመሰንቆና የክራር የበገናንና የዋሽንት የዘፈን ድምፅ በሀገሩ ተሰማ፡፡ ሕዝቡ ወደ ዕቶን እሳት ትጣላለህ ከሚል ማስፈራሪያ ጋር ስሜቱን የሚነካ ሙዚቃም ሲሰማ ያለማመንታት ታዘዘ፡፡ በዚህ አዋጅ ምክንያት በድፍን ባቢሎን የሚኖሩ እስራኤላዊያንም ጭምር ሁሉም ለወርቁ ምስል ሰገዱ፡፡

የአውራጃ ሹመኞች የሆኑት የቤተ መንግሥት ጾመኞች ሦስቱ ወጣቶች ግን አልሰገዱም፡፡ ሁሉም ሲሰግድ አለመስገድ ፣ ሁሉም ሲያጨበጭብ እጅን መሰብሰብ ፣ ሁሉ ሲስቅ መኮሳተር ጽናት የሚጠይቅ ነው፡፡ ‹ከሀገሩ የወጣ ሰው እስኪመለስ ድረስ ፤ ቢጭኑት አህያ ቢጋልቡት ፈረስ› ብለው መተረት አልፈለጉም፡፡ ሀገሩ ሁሉ ከሰገደ በእነዚህ ወጣቶች ለይቶ የሚፈርድባቸው ሰው አልነበረም፡፡ ከእስራኤል ወገን ብዙ ሽማግሌዎች ብዙ መጽሐፍ አዋቂዎች አገጎንብሰው ቢሰግዱም እነዚህ ወጣቶች አልሰገዱም፡፡ ‹‹ከእኛ ብዙ የሚያውቁት እነ እገሌ እነእገሌ ከሰገዱ እኛ ለምን እንጠቆራለን? ከሰው ተለይተን ምን እንፈጥራለን? የአውራጃ ገዢ አድርጎ ሾሞን የለ አሁን እንቢ ብንል ውለታ ቢስ መሆን አይሆንብንም? ስገዱ ያለው ለአንድ ጊዜ ብቻ ነው እንጂ ጣዖት አምልኩ አላለንም ፤ እሳት ውስጥ ከምንገባ ይህችን ቀን አጎንብሰን ብናልፋትስ ፣ ዋናው ልብ ነው›› ብለው ራሳቸውን ሊያሞኙ አልፈለጉም፡፡ ሁሉ ባጎነበሰበት ቀን አንሰግድም ብለው ቆሙ፡፡

#የሚያድናችሁ_አምላክ_ማንነው?

ናቡከደነፆር ሦስቱ ወጣቶች እንዳልሰገዱ ሲነገረው ቁጣው ነደደና አስጠራቸው፡፡ ‹‹የምሰማው እውነት ነውን?›› አለ ፤ እንዲያስተባብሉ ዕድል ሲሠጥ፡፡ ‹አሁንም የመለከትና የእንቢልታ የመሰንቆና የክራር የበገናንና የዋሽንት የዘፈን ድምፅ በሰማችሁ ጊዜ  ብትሰግዱ መልካም ነው›› አለ፡፡ መቼም በመጽሐፍ ቅዱስ እንደ ናቡከደነፆር የሙዚቃን ስሜት ቀስቃሽነት የተረዳ ሰው ያለ አይመስልም፡፡ ‹‹በሉ ሙዚቃው ድጋሚ ይከፈትልሃል ትጨፍራላችሁ›› የሚል ይመስላል፡፡ ስገዱ ከማለቱ ሙዚቃውን ስትሰሙ ማለቱ ይገርማል፡፡ ከዚያ ማስፈራሪያ ጨመረበት ‹‹ተደፍታችሁ ላሠራሁት ምስል ብትሰግዱ መልካም ነው፤ ባትሰግዱ ግን በዚያ ጊዜ በሚነድድ እሳት እቶን ውስጥ ትጣላላችሁ፤ ከእጄስ የሚያድናችሁ አምላክ ማን ነው? ብሎ ተናገራቸው።

ከእጄስ የሚያድናችሁ አምላክ ማን ነው? ለሚለው ለንጉሡ ጥያቄ ሦስቱ ወጣቶች ‹‹ናቡከደነፆር ሆይ በዚህ ነገር እንመልስልህ ዘንድ አስፈላጊያችን አይደለም›› አሉት፡፡ ምን ማለታቸው ነው? ለምን አይመልሱለትም? ይህንን ያሉበት ምክንያት ናቡከደነፆር ከጥቂት ጊዜ በፊት ሕልም አልሞ በተፈታለት ጊዜ ደስ ብሎት ‹‹አምላካችሁ የአማልክት አምላክ የነገሥታትም ጌታ ምሥጢርም ገላጭ ነው›› ብሎ መስክሮ ስለነበር ነው፡፡ (ዳን 2፡47) አሁን ደግሞ ተገልብጦ ‹ከእጄስ የሚያድናችሁ አምላክ ማን ነው?› አላቸው፡፡ ስለዚህ ሦስቱ ወጣቶች ትናንት ያመሰገነውን አምላክ እንደማያውቀው ሲሆን ላንተ መልስ አያስፈልግህም አሉት፡፡ አንዳንድ ሰዎች ትናንት ያመለኩትን አምላክ ዛሬ እንደማያውቁ ሆነው ሲጠይቁ ፣ ትናንት ያመኑበትን ዛሬ ክደው ሲያናንቁ ‹‹በዚህ ነገር እንመልስላቸው ዘንድ አስፈላጊያችን አይደለም››
Ďň_ťėŕėfê_ŧëšfãýê @webzema:
ለነገሩ ለወላዋዩ ናቡከደነፆር ምን መልስ ይሠጣል፡፡ ታሪኩን ስናነብ እንደ ናቡከደነፆር ተገለባባጭ ሰው የለም፡፡ ትንቢተ ዳንኤል  ምዕራፍ ሁለት ላይ ለፈጣሪ መሰከረ ፣ ምዕራፍ ሦስት ላይ ካደ ፣ ምዕራፍ ሦስት መጨረሻ ላይ አምኖ መሰከረ ፣ ምዕራፍ አራት መጀመሪያ ላይ ለፈጣሪ እንደ መዘመር ቃጣው በሕልሙ መልአክ እስከማየት ደርሶ ስለ ፈጣሪ ኃያልነት መሰከረ ፣ ምዕራፍ አራት መጨረሻ ላይ ግን ‹‹ይህች በጉልበቴ ብርታት ለግርማዬ ክብር የሠራኋት ታላቂቱ ባቢሎን አይደለችምን?›› ብሎ ተኮፍሶ እንደ እንስሳ ሣር እስኪግጥ ድረስ ተቀጥቷል፡፡ ስለዚህ ሦስቱ ወጣቶች ‹አምላካችሁ ማን ነው?› ሲላቸው መልስ ልንሠጥህ አያስፈልገንም ፤ አንተው ማን እንደሆነ ሣር ስትግጥ ታየዋለህ አሉት፡፡ እግዚአብሔር ማን ነው ያሉ እነፈርኦን የደረሰባቸው ባይገባህ አንተ ላይ ደርሶ ታየዋለህ ሲሉ ‹እንመልስልህ ዘንድ አስፈላጊያችን አይደለም› አሉት፡፡

ሦስቱ ወጣቶች አምላካችሁ ማን ነው የሚለውን ባይመልሱም ይህንን ግን አሉ ‹‹ንጉሥ ሆይ አምላካችን ከሚነድደው ከእቶኑ እሳት ያድነን ዘንድ ይችላል ከእጅህም ያድነናል› ንጉሥ ሆይ አምላካችን ኃይሉ ከእሳት በላይ ነው፡፡ ያለ እሳት ማንደድ ያለ ውኃ ማብረድ ይችላል፡፡ ከእሳቱ ያድነናል ፤ ‹ከእሳቱ ቢያድናችሁ ምን ዋጋ አለው ፤ ከእሳት ብታመልጡ ከእኔ አታመልጡም› ብለህ ታስብ እንደሆን ‹‹ከእጅህም ያድነናል›› አሉት፡፡

‹‹ነገር ግን ንጉሥ ሆይ እርሱ ባያድነንም አማልክትህን እንደማናመልክ እወቅ›› አሉት፡፡ ወጣቶቹ ‹ባያድነንም› ያሉት ተጠራጥረው አይደለም፡፡ ለጣዖት ከመስገድ ሞት ይሻለናል፣ ለጣዖት በመስገድ የምንጎዳው ጉዳት በእሳት ተቃጥለን ከምንጎዳው አይብስም ፣ የዘላለም እሳት ከሚፈጀን የአንተ እሳት ቢፈጀን እንመርጣለን ለማለት ነበር፡፡ በዚያ ላይ ሦስቱ ወጣቶች ‹ያድነን ዘንድ ይችላል› አሉ እንጂ ‹እንድናለን› አላሉም፡፡ የፈጣሪያቸውን የማዳን ኃይል በእርግጠኝነት ተናገሩ እንጂ ከዚህ እሳት እንደሚድኑ በእርግጠኝነት አልተናገሩም፡፡ ይህም ከትሕትናቸው የተነሣ ነበር፡፡ እግዚአብሔር መላእክቱን ስለ እኔ ያዝዝልኛል ያድነኛል ብሎ ወደ ሞት ራስን መሥጠት ጌታችን ለዲያቢሎስ እንዳለው ጌታ አምላክን መፈታተን ነው፡፡ ስለዚህ ሦስቱ ወጣቶች ‹ባያድነን እንኳን› ሲሉ ምግባራችን ከልክሎት ባያድነን እንኳን ያልዳነው በኃጢአታችን ነው እንጂ አምላካችን ማዳን ተስኖት እንዳይመስልህ አሉት፡፡ 

እነዚህ ወጣቶች ምንኛ ያስደንቃሉ ፤ ስለ ትንሣኤ ሙታን ባልተሰበከበት በዚያ ዘመን ፣ ምንም እንኳን ሥቃይ የማይነካቸው ቢሆንም እንኳን ጻድቃንም ቢሆኑ ወደ ሲኦል በሚወርዱበት በዚያ ዘመን ተስፋ ሳይኖር ተስፋ አድርገው እንደ ሐዲስ ኪዳን ሰው ወደ ሞት የሔዱት እነዚህ ወጣቶች ምንኛ ክቡራን ናቸው፡፡ ለዚህም ነው ሰማዕቱ ዮስጦስ (Justine the martyr) ‹‹ከክርስቶስ በፊት የነበሩ ክርስቲያኖች›› (Christians before Christ) የሚላቸው፡፡

#መርጦ_የሚያነድ_እሳት

ናቡከደነፆር በወጣቶቹ መልስ እጅግ ተበሳጨ ፤ የሚነድደውን እሳት ሰባት እጥፍ እንዲያደርጉት አዘዘ፡፡ ልፋ ሲለው ነው እንጂ እሳቱ ሰባት እጅም ቢሆን ፣ አንድ እጅም ቢሆን ለሦስቱ ወጣቶች መቃጠል ያው መቃጠል ነው፡፡ የባቢሎንን ማገዶ ከማባከን በቀር ሦስቱ ወጣቶች የሚሞቱት ሞትም ያው አንድ ሞት ነው፡፡ የተፈለገው ግን እንዲፈሩ ነበር፡፡ ሰይጣን አሠራሩ እንዲህ ነው ፤ እምነታችን ሲጨምር እሳቱ ሰባት እጥፍ ይጨምራል፡፡ ‹ያድነናል› የሚለው ምስክርነታችን ናቡከደነፆሮችን ያስቆጣል፡፡ በሥልጣናቸው የሚነድደውን እሳት መጨመር እንጂ የእኛን እምነት መቀነስ አይችሉም፡፡ ሦስቱን ወጣቶች ከሰናፊላቸው ፣ ከቀሚሳቸውና ከመጎናጸፊያቸው ከቀረው ልብሳቸውም ጋር እንዲታሠሩ ተደረገ፡፡ ያ ሁሉ ልብስ አብሮአቸው እንዲታሰር የተፈለገው ሥቃያቸውን የበለጠ ለማብዛት ፣ እግራቸው መታሰሩም ሳይንፈራገጡ እንዲቃጠሉ ለማድረግ ነበር፡፡ በዚህ አሰቃቂ ሁኔታ ሦስቱን ወጣቶች ወደ እሳት ጨመሯቸው፡፡ ከእሳቱ ኃይል የተነሣ ‹የጣሏቸውን ሰዎች የእሳቱ ወላፈን ገደላቸው›

ሦስቱን ወጣቶች እሳት ውስጥ ሲገቡ ከእስራቸው ተፈትተው ሲመላለሱ ታዩ ፤   ናቡከደነፆር ባላዋቂ አነጋገር ‹የአማልክት ልጅ› ያለውን ‹የእግዚአብሔር ልጆች› ተብለው ከሚጠሩት መላእክት አንዱ የሆነውን መልአኩን ልኮ የእሳቱን ኃይል አጠፋ፡፡ ‹የእግዚአብሔር መልአክ በሚፈሩት ዙሪያ ይሠፍራል ያድናቸውማል› የተባለውም ተፈጸመ፡፡ ‹የአማልክት ልጅ› የተባለው የመልአኩ መውረድ የወልደ እግዚአብሔር የኢየሱስ ክርስቶስ ምሳሌ ፣ የመምጣቱና የሰውን ልጅ ከሲኦል እሳት የማዳኑ ሥራ ምሳሌ ሆኖ ይኖራል፡፡

ሦስቱ ወጣቶች ልብስ አልብሰው የጨመሯቸው እንዲሰቃዩ ነበር ፤ ሆኖም ለሥቃይ የለበሱት ልብስ ለዝማሬ ሆናቸው፡፡ መቼም ዕርቃን ሆኖ ዝማሬ የለም፡፡ አልብሰው ባይከቷቸው ኖሮ ሲወጡ ዕርቃናቸውን በወጡ ነበር፡፡ የሚያስደንቀው እነዚህ ሦስት ዕፀ ጳጦሶች እንኳን ሊቃጠሉ ጭስ ጭስ እንኳን አይሉም ነበር፡፡
የባቢሎን እሳት አስደናቂ እሳት ነው፡፡ ከእሳቱ ውስጥ እያሉ እሳቱ ያቃጠለው የታሰሩበትን ገመድ ብቻ ነበር፡፡ ከዚያ ውጪ የጣሏቸውን ሰዎች ወላፈኑ ገደላቸው፡፡ ሰዎችን ወደ እሳት መገፍተር ቀላል ነው፤ እሳቱ ግን ገፍታሪዎቹን ሊያቃጥል ይችላል፡፡ ‹‹እሳት በላዒ ለአማፅያን ለእለ ይክህዱ ስሞ ፤ ወእሳት ማኅየዊ ለርቱዓነ ልብ ለእለ ይገብሩ ፈቃዶ›› (ስሙን ለሚክዱ ለአመጸኞች የሚባላ እሳት ነው ፤ፈቃዱን ለሚሠሩ ልባቸው ለቀና የሚያድን እሳት ነው) የሚለው የአባ ሕርያቆስ ቅዳሴ በብሉይ ኪዳን ቢሆን ለባቢሎን እሳት ይሠራ ነበር፡፡

ሦስቱ ወጣቶች እሳት ውስጥ ገብተው የመውጣታቸው ታሪክ በጥላቻና በዘረኝነት እሳት እየነደድን ባለንበት በዚህ ዘመን ሆነን ስንመለከተው መልእክቱ ብዙ ነው፡፡ በሚነድደው እሳት ላይ የእያንዳንዳችን ድርሻ ምንድር ነው? አንዳንድ ሰው ‹ይለይለት ካልደፈረሰ አይጠራም› ይላል፡፡ በስድብ በጥላቻ በነቀፋ ከሩቅም ከቅርብም ሆኖ የሚያባብስ ሰው እንግዲህ እሳቱን ሰባት እጥፍ ከሚጨምሩት የናቡከደነፆር አሽከሮች አይለይም፡፡ በዚያ ላይ ይለይለት ብለህ የምትጨምረው እሳት ወላፈኑ አንተኑ ማቃጠሉ አይቀርም፡፡ ያለነውም የምንኖረውም እሳቱ ውስጥ ሆነው ‹‹የምናመልከው አምላክ ሊያድነን ይችላል›› ብለው በሚጸልዩ ሰዎች ነው፡፡ ጸሎት መፍትሔ ነው ሲባል በሚያስቀን በናቡከደነፆሮች ሳይሆን ዳዊቱን በማያስታጉሉ አናንያ አዛርያና ሚሳኤሎች ነው፡፡

እሳት ውስጥ ገብተው የወጡት እነዚህ አርበኞች ከጸሎቱ ባሻገር አንድ ልብ ነበሩ፡፡ በሙሉ ትንቢተ ዳንኤል ላይ ‹አናንያ እንዲህ አለ ፤ አዛርያም እንዲህ አለ› የሚል አልተጻፈም፡፡ ሦስት ሲሆኑ እንደ አንድ ሰው ሲናገሩ ሲሰሙ ፣ አብረው ሲጾሙ ፣ አብረው ሲሾሙ ፣ አብረው ሲታሰሩ ፣ አብረው ከእሳት ሲገቡ አብረው ሲወጡ ፣ አብረው ሲዘምሩ ነው ያየናቸው፡፡ አንድ ልብ ሳይሆኑ ከእሳት መውጣት አይቻልም፡፡ አናንያና አዛርያ ተፋቅረው ሚሳኤልን ቢጠሉት ኖሮ በሃሳብ ባይስማሙ ኖሮ ተቃጥለው ይቀሩ ነበር፡፡ ‹‹መልአኩን የላከ በእርሱ የታመኑትን ባሪያዎቹን ያዳነ የአናንያ የአዛርያ የሚሳኤል አምላክ ይባረክ›› (ዳን. 3፡28)
መልአኩም እንዲህ አላቸው "እነሆ ለህዝቡ የሚሆን ታላቅ ደስታ የምስራች እነግራችኋለውና "ዛሬ በዳዊት ከተማ መድኃኒት እርሱ ክርስቶስ ጌታ የሆነ ተወልዶላችዃልና አትፍሩ፤ሕጻን ተጠቅልሎ በግርግም ታገኛላችኹ።ሉቃ፪÷፲

እንኳን ለጌታችን ለመድኃኒታችን ለኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በአል በሰላም በጤና አደረሳችሁ መልካም በዓል ይሁንላችው ዘንድ መልካም ምኞቴ ነው።
ዲ/ን ተረፈ ተስፋዬ
@ty1921
@dengel_enate