AddisWalta - AW
45.3K subscribers
41.9K photos
204 videos
20 files
16.6K links
This is Walta Media and Communication Corporate’s official Telegram channel.

For more updates please visit https://shorturl.at/ehosX https://www.youtube.com/c/WaltaTV/featured
Download Telegram
መቐለ

#ከተሞቻችን

በአዲስዓለም ግደይ

የትግራይ ክልል ርዕሰ ከተማ የሆነችው መቐለ ከአዲስ አበባ በስተሰሜን አቅጣጫ በ783 ኪ.ሜ ርቀት ላይ ትገኛለች፡፡ ከባህር ጠለል በላይ በ2 ሺሕ 66 ሜትር ከፍታ ላይ አርፋለች፡፡

መቐለ በዐፄ ዮሀንስ አራተኛ የኢትዮጵያ ዋና ከተማ የነበረች ሲሆን በጨው ንግድ የምትታወቅ ውብ ከተማ ናት፡፡ ከዚህ በተጨማሪም በራስ አሉላ አባ ነጋ የተሰየመ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ ባለቤትም ነች፡፡

500 ሺሕ ገደማ የሚገመት የህዝብ ብዛት ያላት መቐለ ነዋሪዎቿ የተለያዩ ባህላዊ ምግቦች ያላቸው ሲሆን ከእነሱም ውስጥ አንባሻ እና ህብስት ይጠቀሳሉ፡፡

በዚህች ውብ ከተማ ሂፖ የተባለ ባህላዊ መጠጥ ይገኛል፡፡ ይህ መጠጥ የመንግስት ሰራተኛን ግምት ውስጥ በማስገባት ከ10 ሰዓት በፊት አይሸጥም፡፡ በተጨማሪም እንደ ጀርሲ፣ ሽፎን እና ጥልፍ የመሳሰሉ ባህላዊ አልባሳትም የመቐለ ነዋሪዎች መገለጫዎች ናቸው፡፡

በመቐለ ከተማ በተለያዩ ጊዚያት ብዙ አስገራሚ ክስተቶች ተከናውነዋል፡፡
👇👇
https://www.facebook.com/100064690148931/posts/pfbid02PFuWMfmGGTSxBdZv3nW3Y7ydNCWmaiWpik9XHGVAB24U6vwDXYukMasmc6ukXwUul/?mibextid=Nif5oz0
ጎንደር

#ከተሞቻችን

በአዲስዓለም ግደይ

ጥምቀት ሲነሳ ጎንደርም አብራ ትነሳለች፡፡ ጥምቀትና ጎንደር የገጠሙ እለት እንኳንስ ለጎብኝዎች ለከተማዋ ነዋሪዎችም ታይተው አይጠገቡም፡፡

ታሪካዊቷ የጎንደር ከተማ የተቆረቆረችው በ1628 ዓ.ም ነበር። ከአዲስ አበባ በስተሰሜን አቅጣጫ በ640 ኪ.ሜ ርቀት ላይ ትገኛለች::

ጎንደር የፖለቲካ፣ የሃይማኖት እና የንግድ ማዕከል ሆና በርካታ ዓመታትን ከመዝለቋ በተጨማሪ የሀገሪቱ ማዕከላዊ መንግሥት መቀመጫ እና መዲና ነበረች።

አንዳንድ ታሪካዊ መረጃዎች ስሟን ያገኘችበትን መንገድ ሲያብራሩ በ"ጎ" በሚጀምር አካባቢ ማዕከላዊ ከተማ እንደሚከተም ከሚነገር ትንቢት ጋር የተያያዘ እንደሆነ ሲናገሩ አንዳንዶች ደግሞ "ከጎን እደር" ከሚለው ንግግርና ታሪክ ጋር ያዛምዱታል።

የሕዝብ ቁጥሯ ከ480ሺህ በላይ የሚገመተው ጎንደር የአፄ ፋሲልን ጨምሮ በርከት ያሉ አብያተ መንግሥታት ያሏት ከተማ ናት::

ጎንደር በእንግዳ ተቀባይነት፣ በሃይማኖት እና በውብ የኪነ ጥበብ ሀብቶቿ የምትጠቀስ ውብ ከተማ እና የ44 ታቦታት መገኛ ናት::

ፒያሣ፣ አራዳ፣ ቼቼላ፣ ብልኮ፣ አውቶ ፓርኮ እና ሌሎች ስመገናና የሰፈር ስሞች አሏት።
https://www.facebook.com/wmccwaltamediaandcommunicationcorporate/posts/pfbid0MX12TyggHJQW6uu6xAvzSP8DNRbi8oGgQi3X2HfxVsxXPPKgwpXZQdJV3jVG2aAYl
#ከተሞቻችን
#ደሴ

በአዲስዓለም ግደይ

የፍቅር ሀገር የቆንጆዎች መፍለቂያ የሆነችው ደሴ ከተማ ከአዲስአበባ በስተሰሜን አቅጣጫ 400 ኪ.ሜ ርቀት ላይ ትገኛለች፡፡ ከባህር ጠለል በላይ 2 ሺሕ 550 ሜትር ላይ ያረፈች ሲሆን በ1882 ዓ.ም እንደተቆረቆረች ይነገራል።

ደሴ በአማራ ክልል በደቡብ ወሎ ዞን የምትገኝ ሙስሊምና ክርስትያኑ በአንድነት የሚኖርባት የወይና ደጋ አየር ፀባይ ያላት ከተማ ናት።

የአካባቢዋ መሬት ከእሳተ ጎመራ ቅሪት የሚመነጭ ስለሆነ በንጥረ ነገር የዳበረ እና ለምነት እንዳለው ይነገራል።

ከዚህ በተጨማሪ በአስደናቂው ጦሳ እና አዝዋ ተራሮች ተከባ ይበልጥ ድምቀትን ተጎናፅፋለች።

የንጉስ ሚካኤል ቤተመንግሥት አይጠየፍ አዳራሽ፣ ደሴ ሙዚየም፣ አልጋወራሽ ቤተመንግስት፣ ሸዋበር መስጊድ፣ ደሴ ደብረ መድሃኒት መድሃኒዓለም ቤተ ክርስትያን እና ሎሎችም ታሪካዊ ቦታዎች አሏት።

አንደኛና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት እንዲሁም ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ሲኖሯት ወይዘሮ ስህን፣ ወሎ ዩኒቨርስቲ፣ መምህር አካለወልድ፣ እና ሆጤ ጥቂቶቹ ናቸው።

አንዳንድ ታሪካዊ መረጃዎች ስሟን ያገኘችበትን መንገድ ሲያብራሩ ሰኞ ገበያ እየተባለ በሚጠራው አካባቢ ጠላ በመሸጥ የሚተዳደሩ "ደሴ" ከሚባሉ እናት ጋር የተያያዘ ነው ሲሉ አንዳንዶች ደግሞ "ደስዬ" ወይም "የኔ ደስታ" ከሚለው ጋር ያያይዙታል።

እንደ ማሪቱ ለገሰ፣ ዚነት ሙሃባ፣ ያሲን ሙሃመድ እና ሌሎችም ብዙ ታላላቅ ድምፃውያን ከደሴ እና አካባቢዋ ወተዋል።

ከዚህች የቆንጆዎች መፍለቂያ ተወልዳችሁ ያደጋችሁ እና ልዩ ትዝታ ያላችሁ ትዝታችሁን ብታጋሩን መልሰን ወደናንተ እናደርሳለን።

መልካም ሳምንት!!!
#ከተሞቻችን
ጅማ

በአዲስዓለም ግደይ

በምዕራብ ኢትዮጵያ ከሚገኙት ከተሞች ጅማ በስፋት ትልቋ ስትሆን ከተማዋ በ1880 ዓ.ም እንደተቆረቆረች ይነገራል፡፡ የቆረቆሯት፣ ያስፋፏትና ዝነኛ ያደረጓት በዲፕሎማሲ ጥበባቸው ተጠቃሽ የሆኑ ንጉስ አባጅፍር እንደሆኑ መረጃዎች ያመለክታሉ።

የጅማ ከተማ የአባጅፋር ቤተ መንግሥትን ጨምሮ ሙዚየም፣ ኢንዱስትሪ፣ ፓርክ፣ ዩኒቨርሲቲ፣ አየር ማረፊያ፣ ኮሌጆች እንዲሁም የገበያ ማዕከሎችና ሌሎች ይገኙባታል።

ከሃይማኖት ተቋማት ደግሞ ሙኒር፣ ቶፊቅ፣ ዛውያ፣ ሙጃሂድ፣ ፈቲ፣ ራማ፣ አባቦቃ መስጊድ እንዲሁም የማርያም፣ የሚካኤል፣ የመድኃኒዓለም፣ የእየሱስ እና የገብርኤል ቤተክርስቲያናት የሚጠቀሱ ናቸው።

የጅማ ከተማ በተደጋጋሚ በድምጻዊያን ከተዘፈነላቸው ከተሞች አንዷ ስትሆን ንዋይ ደበበን ጨምሮ ተወዳጁ ድምጻዊ የነበረው ሀጫሉ ሁንዴሳ ዘፍነውላታል።
👇👇
https://www.facebook.com/wmccwaltamediaandcommunicationcorporate/posts/pfbid02LhB3ADj3LQhBd8C7C82WvGVeQabvU6Ao4sGi7j75vjst4fzyRTsKMYiRLuGhyMnrl
#ከተሞቻችን
የምድር ገነት! አርባምንጭ

የስሟ መጠሪያ ከግርጌዋ ከተዘረጋው ሰፊ ጥቅጥቅ ደን ውስጥ የመሸጉት 40 እና ከዚያም በላይ የሆኑት ምንጮቿ ናቸው። ተፈጥሮ ያለስስት ልግስናዋን የቸረቻት የምድር ገነት ተምሳሌት ናት ቢባል ማጋነን አይሆንም። የስራ ጥረት መገለጫ እና የጥበበኞች መፍለቂያ ምድርም ናት...... አርባ ምንጭ!

ከ1960 ዓ.ም በፊት በፊትአወራሪ አእምረስላሴ አበበ እንደተቆረቆረች የሚነገርላት አርባምንጭ ከአዲስ አበባ በደቡብ አቅጣጫ 505 ኪ.ሜ ርቀት ላይ ትገኛለች፡፡ አርባምንጭ በታላቁ የምስራቅ አፍሪካ ስምጥ ሸለቆ ዉስጥ በተራሮች ተከባ በ1 ሺሕ 285 ሜትር የባህር ጠለል ከፍታ ላይ ትገኛለች።

ቆላማ የአየር ንብረት ያላት ሲሆን የሙቀት መጠኗ በአማካኝ 29 ዲግሪ ሴንቲግሬድ ይለካል። የአርባምንጭ ከተማ የሴቻ ከተማ አስተዳደር ማዕከል እና በ 4 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የሲቀላ ከተማ የንግድ እና መኖሪያ አካባቢዎችን ያቀፈ ነው።

የአርባምንጭ ከተማ ነጭ ሳር ብሔራዊ ፓርክን ጨምሮ የአርባዎቹ ምንጮች እና የሁለት ታላላቅ ሐይቆች፤ ማለትም አባያ እና ጫሞ መገኛም ናት። የደፈረሰ መልክ ያለው የአባያ ሀይቅ ከስምጥ ሸለቆ ሀይቆች በስፋት ትልቁ ሲሆን ጥልቀቱም 13 ሜትር ነዉ። በአባያ ሀይቅ ላይ ከ 11 በላይ የሚሆኑ ከአለት የተዋቀሩ ደሴቶች ይገኛሉ።

ሙሉውን ለማንበብ ቀጣዩን ማስፈንጠሪያ ይጫኑ
https://shorturl.at/jCEFT
ሰመራ

#ከተሞቻችን

በዛሬው በከተሞቻችን ዝግጅት ወደ ሰመራ ከተማ ዘልቀናል፡፡ ሰመራ የአፋር ክልል ዋና ከተማ ስትሆን ከአዲስ አበባ 594 ኪ.ሜ ርቀት ላይ ትገኛለች፡፡

የድንቅ ባህል እና እሴት መገለጫ ፣የሰሜን ምስራቋ ውብ መዳረሻም ናት ሰመራ።

ከሞቃታማ ቦታዎች አንዷ መሆኗ የሚነገርላት የሰመራ ከተማ ከመስከረም እስከ መጋቢት ባለው ጊዜ ውስጥ የሙቀት መጠኗ እስከ 48 ዲግሪ ሴሊሼዬስ እንደሚደርስ ይገለጻል፡፡
ሠመራ የተለያዩ ብሔር ብሔረሰቦች ተዋደውና ተከባብረው የሚኖሩባት ከተማ ስትሆን የክልሉ ማህበራዊ፣ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ማዕከልም ናት፡፡ በዚህም በአጭር ጊዜ ውስጥ እድገት በማሳየት ላይ ካሉ ከተሞች ተርታ ስሟ ይነሳል።

የሰመራ ከተማ መገኛ የሆነው የአፋር ክልል ወርቅን ጨምሮ ፖታሽየም፣ሰልፈር፣ ፎስፈረስ እና ሌሎችም የተለያዩ ማዕድናት መገኛ ነው።ከፍተኛ የሆነው የአገራችን የጨው ምርት የሚገኘውም በዚሁ የአፋር ክልል ነው።

የአፋር ስምጥ ሸለቆ የታላቁ ስምጥ ሸለቆ አካል ሲሆን የጥንታዊ የሰው ልጅ ቅሪተ አጽምና ይጠቀምባቸው የነበሩ የድንጋይ መሳሪያዎች የሚገኙበት ስፍራ ነው፡፡ ለዘህም የሉሲን ቅሪተ አፅም ጨምሮ ሌሎች የተለያዩ የአርኪዮሎጂ ግኝቶች ይጠቀሳሉ።

የአዋሽ ብሄራዊ ፓርክ ከሰመራ ከተማ ወጣ ብሎ የሚገኝ ሲሆን በአካባቢው ካሉት የቱሪስት መስህቦች አንዱ ነው። ፓርኩ ዝንጀሮዎች፣ ዋርቶግ እና በርካታ የአእዋፍ ዝርያዎችን ጨምሮ በተለያዩ የዱር እንስሳት ይታወቃል።
👇👇
https://m.facebook.com/story.php?story_fbid=pfbid0zxzi3og6iBZViGUQSAgfpUZ8p1SqGhHj1YzaKLcghqDGWb37vDmcnBGsYY9Htxibl&id=100064690148931&mibextid=UyTHkb
#ሀዋሳ ውቧ ከተማ
#ከተሞቻችን

በ1952 ዓ.ም በአፄ ኃይለስላሴ ዘመነ መንግስት እንደተመሰረተች ይነገራል፡፡ የስሟ ስያሜ ምክንያት የሆነው የሀዋሳ ሀይቅ ከከተማዋ ምዕራብና ሰሜን ምዕራብ አቅጣጫ ተንጣሎ የሚገኝ ውብ የተፈጥሮ መስህብ ነው፡፡

"ሀዋሳ" የሚለው የሲዳምኛ ቃል ሲሆን "ትልቅ ወይም ሰፊ የውሃ አካል" በሚል የአማርኛ ፍቺ ይተረጎማል።

ሀዋሳ የሲዳማ ክልላዊ መንግስት አስተዳደር ዋና መቀመጫ ስትሆን ከአዲስ አበባ በ275 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ትገኛለች፡፡

ከባህር ጠለል 1 ሺሕ 708 ሜትር ላይ የምትገኘው ሀዋሳ የአየር ንብረቷ ለኑሮ ምቹ መሆኑም ይገለጻል፡፡ ውበት፣ ፅዳት እና ፍቅር የከተማዋ ልዩ መገለጫዎችም ናቸው።

የሀዋሳ ከተማ በፍጥነት እያደጉ ካሉ ከተሞች አንዷ ስትሆን ስምንት ክፍለ ከተሞች እና 32 የገጠር ቀበሌዎችን አቅፋ ይዛለች።  

ከፍተኛ የቱሪስት ፍሰት የሚታይባት ሀዋሳ ታላላቅና ዓመታዊ የገብርኤል ንግስ በዓል እና የሲዳማ ዘመን መለወጫ የሆኑትን "ፊቼ ጫምባላላ" በድምቀት የምታስተናግድ ከተማም ነች።

በከተማዋ ከሚገኙ ተቋማት መካከል የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ፣ የሀዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ አና የሲዳማ ባህላዊ ሙዚየም የሚገኙ ሲሆን በተጨማሪም እንደ ኃይሌ፣ ሌዊ እና ሴንትራል ሀዋሳን የመሳሰሉ ሪዞርትና ሆቴሎች መገኛም ናት።

የከተማዋ ድምቀት የሆነው የሀዋሳ ሀይቅ በሪፍት ቫሊ ውስጥ ከሚገኙ ሀይቆች አንዱ ነው፡፡ ከፍተኛ የአሳ ምርት የሚታፈስበት እና ጉማሬን ጨምሮ የተለያዩ አዕዋፋት መገኛ ስፍራ ነው፡፡
👇👇
https://m.facebook.com/story.php?story_fbid=pfbid02RtckdWyYouBqyHcKSdYviVGiJwWtxGnBYVsMX5iHyy4SBFMYZtW9DNjeDtaEfybQl&id=100064690148931&mibextid=UyTHkb
ደብረ ብርሀን

#ከተሞቻችን

ደብረ ብርሃን በቀድሞ ስያሜዋ "ደብረ ኤባ" እንደነበረችና በአፄ ዘርዓያዕቆብ ዘመነ መንግስት በ1446 ዓ.ም የተቆረቆረች ጥንታዊት ከተማ መሆኗ ይነገርላታል፡፡

አፄ ዘርዓያዕቆብ በዘመናቸው ባሳነፁት የቅድስት ስላሴ ቤተ መቅደስ (ደብር) ላይ ከሰማይ ብርሃን መውረዱን ተከትሎ "ደብረ ብርሃን" ሲሉ ከተማዋን እንደሰየሟት የታሪክ ድርሳናት ያስረዳሉ።

ከርዕሰ መዲና አዲስ አበባ 130 ኪ.ሜ ርቀት ላይ የምትገኘው ደብረ ብርሃን ከተማ በአማራ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት በሰሜን ሸዋ ዞን አስተዳደር ውብ በሆነ አረንጓዴ መልክዓ-ምድር ከትማለች።

ደጋማ የአየር ንብረት ያላት ከተማዋ ከባህር ወለል በላይ በአማካይ 2 ሺሕ 750 ሜትር ከፍታ ላይ ትገኛለች፡፡ በአብዛኛው ሜዳማ የሆነ ተፈጥሯዊ የመሬት አቀማመጥን የተቸረችም ናት።

ዓመቱን ሙሉ ያለማቋረጥ የሚፈሰው የ"በሬሳ "ወንዝ በከተማዋ መሀል የሚንሸራሸር ተፈጥሯዊ ሀብቷ ሲሆን በተጨማሪም ክረምትን ጠብቀው የሚፈሱ "ዳለቻ" እና "ሙዘይን" ወንዞች በአካባቢዋ ይገኛሉ።
👇👇
https://www.facebook.com/wmccwaltamediaandcommunicationcorporate/posts/pfbid0Bivs9LQL9HKnSZrSCFX9xXr9NaijeezFzUimN35feWfY7Wndyr54VKWphthWikHGl
#አዳማ
#ከተሞቻችን

"የስምጥ ሸለቆ እንቁ" ተብላ የምትሞካሸው የአዳማ ከተማ ከመዲናችን አዲስ አበባ 99 ኪ.ሜ ላይ ትገኛለች፡፡

"አዳማ" የሚለውን ስያሜዋን ያገኘችው "አዳሚ" ከሚለው የአፋን ኦሮሞ ቃል ሲሆን ትርጓሜውም "ቁልቋል" ወይም "የቁልቋል ዛፍ" ማለት ነው፡፡

1 ሺሕ 712 ሜትር ከባህር ጠለል ከፍታ ላይ የምትገኘው ይህች ከተማ ቆላማ የአየር ንብረት ሲኖራት በአብዛኛው ሜዳማ የመሬት አቀማመጥ እና አሸዋማ የአፈር ተፈጥሮ አላት።

የከተማዋ መገለጫ የሆነው "የኦሮሞ ሰማዕታት ሀውልት" ከአባገዳ አዳራሽ ፊትለፊት የሚገኝ ሲሆን ይህም በከተማው መግቢያ ላይ የሚገኝ ነው።

ከተማዋ የንግድ፣ የኢንዱስትሪ፣ የስብሰባ እና የመዝናኛ መዳረሻ በመሆኗ ከፍተኛ እንቅስቃሴ ያለማቋረጥ የሚታይባትም ናት፡፡

የአዳማ ከተማ የመቻቻል፣ የአብሮነት እና በእንግዳ ተቀባይነት ተምሳሌት ተደርጋም ትወሰዳለች።

ለከተማዋ ምስረታ እና መስፋፋት ምክንያት ተደርጎ የሚነሳው የአዲስ አበባ - ጅቡቲ የባቡር መስመር ዝርጋታ ሲሆን ቀደምት ከሆነው የከሰል ባቡር ጀምሮ እስከአሁኑ የኤሌክትሪክ ባቡር ድረስ አንዱ የትራንስፖርቱ መዳረሻ ከተማ ሆናም ታገለግላለች።

በአዳማ ከተማ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የሚገኙ ሲሆን አዳማ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ፣ ዩኒቲ ዩኒቨርስቲ እና ሪፍትቫሊ ዩኒቨርሲቲዎች ይጠቀሳሉ፡፡

የአዳማ ኢንዱስትሪ ፖርክ፣ አዳማ ቆርቆሮ ፋብሪካ እና አዳማ ትራክተር መገጣጠሚያን ጨምሮ የጨርቃጨርቅ እና አውቶሞቲቨ ፋብሪካዎችም በከተማዋ ይገኛሉ።

https://shorturl.at/djs09

በአዲስዓለም ግደይ
አክሱም

#ከተሞቻችን

ከርዕሰ መድና አዲስ አበባ በ1 ሺሕ 24 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የምትገኘው አክሱም ከተማ ወይና ደጋ የአየር ንብረት ያላት ሆና በአብዛኛው ድንጋያማ የመሬት አቀማመጥን ተላብሳለች።

በሀገራችን ቀዳሚ የቱሪስት መዳረሻ የሆነችው አክሱም የተለያዩ የሰፈር ስያሜዎች አሏት፡፡ ከነዚህም መካከል አዲ ክልተ፣ ምቃ ከበሮ፣ ማእሹም፣ ገዛኡግማይ እና ሽርኩይት ይጠቀሳሉ።

የታሪክ ድርሳናት እንደሚያትቱት “አክሱም” የሚለው ስያሜ የሁለት ጥምር ቃላት ውጤት ሲሆን "አኩ" የሚለው አገውኛ ግስ "ውሀ" በሚል ሲተረጎም፣ “ሱም” ደግም የግዕዝ ቋንቋ ሆኖ ትርጉሙም “ሹም” እንደ ማለት ነው፡፡

ጥንታዊቷን "አክሱም ፅዮን" ቤተክርስቲያን ጨምሮ፣ ሐውልቶች እና የነገስታት መቃብሮች እንዲሁም "ጽላተ ሙሴ" በከተማው የሚገኙ ጥንታዊና ታሪካዊ ቅርሶች ሲሆኑ በዩኔስኮ መዝገብ ላይም ሰፍረው ይገኛሉ።

የአክሱም ሐውልት በአክሱም ከተማ የሚገኝ የዓለማችን ረጅሙ ትክል የድንጋይ ሐውልት ነው። ይህ ሐውልት 1700 ዓመታትን ያስቆጠረ ሲሆን የ24 ሜትር (78 ጫማ) ርዝመት አና 160 ቶን ክብደት አለው።

ከተማዋ የአክሱም ዩኒቨርሲቲ ዋና ካንፓስን ጨምሮ 3 የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች፣ 2 የመንግስት ኮሌጆችና 13 የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤቶች አሏት፡፡
👇👇
https://www.facebook.com/wmccwaltamediaandcommunicationcorporate/posts/pfbid02krAHEuxKYJmB22kFqHxDhigCUEKVBgUMc3vYEjZgbiC8TQA4ZwEKrPKtwcWT2Yonl
አንኮበር

#ከተሞቻችን

የአንኮበር ከተማ በ1733 ዓ.ም የሸዋ ማዕከል በመሆን በመርዕድ አዝማች አመሐ እየሱስ እንደተቆረቆረች ይነገራል፡፡ የከተማዋ ታሪካዊ ዳራ መነሻውን የሚያደርገው በ12ኛው ክፍለ ዘመን ከነገሱት ከዐፄ ይኵኖ አምላክ ጀምሮ ነው።

የአንኮበር ከተማ ደጋማ የአየር ንብረት ሲኖራት ለተለያዩ አትክልትና ፍራፍሬ እድገት ምቹ የሆነ የአፈር ተፈጥሮም አላት።

አንኮበር በተለያዩ ወቅቶች በሸዋ ለተቀመጡ ነገስታት በማዕከላዊ ከተማነት እንዳገለገለች የታሪክ ድርሳናት ያስረዳሉ።

አንኮበር ከመዲናዋ አዲስ አበባ በ172 ኪሎ ሜትር እንዲሁም ከደብረ ብርሃን በ42 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ትገኛለች። ከባህር ጠለል በላይ 3 ሺሕ 700 ሜትር ከፍታ ላይም ትገኛለች።

የአፄ ምኒልክ የትውልድ ስፍራ የሆነችው አንኮበር በጣሊያን ጦር ውድመት ደርሶባት ነበር፡፡ የአፄ ምኒልክ ቤተመንግስት ዳግም አድሶ በመገንባትም ታሪካዊ አሻራን ማቆየት የቻለች ከተማ ናት አንኮበር። ከእድሳቱ በኋላም ቤተ መንግስቱ በየዓመቱ ከ30 ሺሕ እስከ 40 ሺሕ ሰዎች ይጎበኛል።

ከተማዋ በአንኮበር ቤተመንግስት ከሚጎበኙ ሰው ሰራሽ ቅርሶች በተጨማሪ ተፈጥሯዊ መልክዓ ምድር እና ብርቅዬ የሆኑ ዕፅዋት የስፍራው ማራኪ ገፅታዎች ናቸው።
👇👇
https://www.facebook.com/wmccwaltamediaandcommunicationcorporate/posts/pfbid0ph4cVfPJVLu8Jd71b6KSVtMoV47tm6HGnyjPYzJLMFrBzas5TN5qSSA2oQC3zMsDl
ድሬዳዋ

#ከተሞቻችን

አንድ ክፍለ ዘመን የተሻገረ እድሜ ያላት ተግባቢና ሰው ወዳድ ማህበረሰብን አቅፋ የያዘች የፍቅር ከተማ ናት ድሬዳዋ፡፡

ከተማዋ ከርዕሰ መዲና አዲስ አበባ በስተምስራቅ አቅጣጫ 459 ኪ.ሜ ርቀት ላይ ትገኛለች፡፡ ከባህር ጠለል በላይ 1 ሺሕ 276 ሜትር ከፍታ ላይ የምትገኘው ድሬዳዋ ቆላማ የአየር ንብረት ሲኖራት አሸዋማ የመሬት ተፈጥሮን የተላበሰች ናት።

ድሬ እየተባለች የምትጠራው ድሬዳዋ የፍቅር ሀገር በሚል ተምሳሌታዊ አጠራርም ትወከላለች። ድሬ በርከት ካሉ ሰፈሮቿ ስያሜያቸው ለየት ያሉ የሰፈር ስሞች አሏት፡፡ ከነዚህ ውስጥ ሳቢያን፣ ገንደቆሬ፣ ለገሀሬ፣ ታይዋን፣ አሸዋ ሜዳ እና ከዚራ ይጠቀሳሉ።

በዛፍ ጥላዎቿ የምትታወቀው ከዚራ ሰፈርን የገበያ መቀመጫ ከሆነው መጋላ የሚለየው "የደቻቱ ወንዝ" በከተማዋ አማካኝ ስፍራ ላይ የሚገኝ የተፈጥሮ ገፅታ ነው።👇👇
https://www.facebook.com/wmccwaltamediaandcommunicationcorporate/posts/pfbid0LPeHeGWftLtFb1FnZ7oaKG68mm24Ss1F9wvdVbj5NcRppHf2bxDsbU6Kv6wwN4M4l
ሚዛን አማን

#ከተሞቻችን

የሚዛን አማን ከተማ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል አንዷ መቀመጫና የቤንች ሸኮ ዞን ዋና መቀመጫ ሆና በማገልገል ላይ ትገኛለች፡፡

ከተማዋ ከርዕሠ መድናችን አዲስ አበባ በ568 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የምትገኝ ስትሆን በ1930 ዓ.ም እንደተቆረቆረች ይነገራል።

ሚዛን አማን ከተማ የቀድሞ ሚዛን ተፈሪ የሚለውን ስያሜ ያገኘችው በንጉሱ አፄ ኃይለስላሴ ዘመነ መንግሥት አካባቢውን እንዲያስተዳድሩ ተሹመው በተላኩት በእንደራሴው ፊታውራሪ አለማየሁ ፍላቴ መሆኑ ይነገራል፡፡

የንጉስ አፄ ኃይለስላሴ ልደት እየተከበረ በነበረበት ወቅት ከተማዋ በመመስረቷ የልደት መታሰቢያ ለማድረግ እንደሆነም ታሪክ ይጠቅሳል።

በ1ሺሕ 451 ሜትር ከባህር ጠለል በላይ ከፍታ ላይ የምትገኘው ሚዛን አማን በአረንጓዴ መልክዓ ምድር የተሸፈነች እና ወይናደጋ የአየር ንብረት ያላት ከተማ ነች።

እምቅ የተፈጥሮ ሀብት ያላት ሚዛን አማን በዙሪያዋ ከፍተኛ የደን ክምችት ያላት ሲሆን ቡናን ጨምሮ፣ በፍራፍሬ እና በቅመማቅመም ምርቶች ትታወቃለች፡፡ የአረንጓዴ ልማት ፈርጥ ተብላም ትጠራለች።
https://www.facebook.com/wmccwaltamediaandcommunicationcorporate/posts/pfbid0NMmjbVppnwZjZ9NxBEeKkDnjSQ26t2A9oaG6xmD6MCFc7FEwdAG1pXAJxreKrLnJl
#ከተሞቻችን
አሶሳ

"የወርቅ ምድር" በሚል የምትሞካሸው አሶሳ ከተማ በ1929 ዓ.ም በንጉስ ሼህ ሆጀሌ አልሀሰን የተቆረቆረች ሲሆን የቤንሻጉል ጉምዝ ክልላዊ መንግስት ዋና መቀመጫ ናት።

ከመዲናችን አዲስ አበባ በስተሰሜን ምዕራብ አቅጣጫ 687 ኪ.ሜ ርቀት ላይ የምትገኘው አሶሳ ከባህር ጠለል በ1570 ሜትር ከፍታ አላት፡፡

አሁን ያለውን ስያሜ ከማግኘቷ በፊት "አጾጾ" ተብላ ትጠራ የነበረ ሲሆን "አሶሳ" ብለው የሰየሟት ሼህ ሆጀሌ እንደሆኑ እና ትርጓሜውም “መሰባሰብ” የሚል እንደሆነ ታሪኳ ያስረዳል።

ቆላማ የአየር ንብረት ያላት አሶሳ የቀርከሃ ተክልን ጨምሮ ማንጎ፣ ጥጥ፣ ብርቱካን፣ ሸንኮራ አገዳ እና የጎማ ዛፍ አብቃይ ምድር ስትሆን በእምነበረድ እና ወርቅ ምርቶቿም ትታወቃለች።

ሙሉውን ለማንበብ ቀጣዩን ማስፈንጠሪያ ይጫኑ
https://www.facebook.com/wmccwaltamediaandcommunicationcorporate/posts/pfbid047Xv3sxW13EfVL4wYFHQh54QgeAtg35pmVD8EoTuMimPYRo4Pq5oQoK4BkKFyceLl
ሻሸመኔ
#ከተሞቻችን

የምዕራብ አርሲ ዞን ዋና መቀመጫ የሆነችው የሻሸመኔ ከተማ ከአዲስ አበባ በስተደቡብ አቅጣጫ 255 ኪ.ሜ ርቀት ላይ የምትገኝ ሲሆን በ1913 እንደተቆረቆረች ይነገርላታል።

ከከተማዋ ስያሜ ጋር በተያያዘ እንደ አፈታሪክ የምትነሳ አንዲት "ሻሼ" የምትባል እንግዳ ተቀባይ ሴት በአካባቢው ትኖር እንደነበር እና የሻሼ ቤት ወይም በኦሮምኛ "መነ-ሻሼ" የሚለው የስፍራው ስያሜ በጊዜ ሂደት ተቀይሮ ሻሸመኔ እንደተባለ በታሪክ ይወሳል።

ወይና ደጋ የአየር ንብረት ያላት የሻሸመኔ ከተማ ከባህር ጠለል በላይ 1937 ሜትር ከፍታ ላይ ትገኛለች።

ጀምበር የማይጠልቅባት የሻሸመኔ ከተማ የዞኑ ዋና የንግድ እና የትራንስፖርት ማዕከል ስትሆን ሐዋሳን ጨምሮ ወላይታ እና ዲላን የምታገናኝ ባለ5 በር ኮሪደር ከተማ ነች።

የተለያዩ ብሄረሰቦችን በጉያዋ ያቀፈችው ሻሸመኔ በ12 ወረዳ እና 4 ክፍለ ከተማዎች የተዋቀረች ስትሆን አቦስቶ፣ ጎፋ፣ አዋሾ፣ ኩዬራ እና አራዳ ከሰፈር ስያሜዎቹ መካከል ተጠቃሾች ናቸው።

ከበሀማስ፣ ከኮቤኮ፣ ከካሪቢያን እና ከጃማይካ የመጡ ዜጎች ለበርካታ ዓመታት ከትመው የሚኖሩባት ከተማ እንደሆነችም ይነገርላታል።

በከተማዋ ሻሸመኔ ሙዚየምና የተለያዩ የትምህርት ተቋማት የሚገኙ ሲሆን ከነዚህም ውስጥ ሊድ ስታር ኢንተርናሽናል አካዳሚ፣ ሉሲ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት፣ ሚሊኒየም ሻሸመኔ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት፣ እናት ኮሌጅ እና የሻሸመኔ ፖሊቴክኒክ ኮሌጅ ይገኙበታል።
👇👇
https://www.facebook.com/wmccwaltamediaandcommunicationcorporate/posts/pfbid0tqnYZqVyqH8k4ni2NZqrG57kTBLcjgagtMR986bCEyGm6CVVHv7gsMjX8ct6TbNpl
#ከተሞቻችን
ዓዲግራት

በ14ኛው ክፍለ ዘመን እንደተቆረቆረች የሚነገርላት ታሪካዊቷ የዓዲግራት ከተማ ከመዲናችን አዲስ አበባ በስተሰሜን አቅጣጫ 1ሺሕ 38 ኪ.ሜ ርቀት ላይ ትገኛለች፡፡

የአመለሸጋ ሕዝብ መገኛ፣ የአብሮነት ማሳያና በእንግዳ አክባሪነቷ ተምሳሌት የሆነች ከተማ ናት፡፡

ከተማዋ ከባሕር ጠለል በላይ 2 ሺሕ 457 ሜትር ከፍታ ላይ የምትገኝ ሲሆን ደጋማ የአየር ፀባይ አላት፡፡

ለከተማዋ ስያሜ የሆነውና "ዓዲግራት" የሚለው ቃል ትግርኛ ሲሆን ትርጓሜውም "የእርሻ መሬት ሀገር" እንደ ማለት ነው።

በ6ኛው መቶ ክፍለ ዘመን እንደተገነባ የሚነገርለት "ደብረ ዳሞ" እና የ"ጉንዳ ጉንዶ" ገዳማት በዓዲግራት አካባቢ የሚገኙ የቱሪስት መዳረሻዎች ናቸው፡፡

የከተማዋ ተወላጆች ከየአሉበት ተሰባስበው ከወላጆቻቸው ጋር የመስቀል እና የአረፋ በዓላትን በድምቀት የሚያከበሩባት ከተማ ነች።

ሙሉውን ለማንበብ ተከታዩን ማስፈንጠሪያ ይጫኑ👇👇
https://www.facebook.com/wmccwaltamediaandcommunicationcorporate/posts/pfbid0AJQXDKAqaHh6RecyrUZ85bL8CvqapPPVVEJrhjcTUR4XzYDDCKNa1SBB5HEkEGQgl
ዲላ
#ከተሞቻችን

የአረንጓዴው ምድር የጌዴኦ ዞን አስተዳደር ከተማና የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የክላስተር ከተሞች አንዷ የሆነችው ዲላ ከመዲናችን አዲስ አበባ በደቡብ አቅጣጫ 365 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ትገኛለች፡፡

የፍቅር፣ የመተሳሰብ፣ የሰላም እና የአብሮነት ተምሳሌት የሆነችው ዲላ ከተማ በ1904 ዓ.ም ገደማ በቀድሞ የሲዳማ ሀገር ገዥ ባራምባራስ ደቻ ኡዶ እንደተቆረቆረች ይነገራል። ምስረታዋም ከቀረጥ ኬላ መከፈት ጋር ተያይዞ እንደሆነ መረጃዎች ይጠቁማሉ።

ቆላማ የአየር ንብረት ያላትና ነፋሻማዋ የዲላ ከተማ 1 ሺሕ 570 ሜትር ከባህር ጠለል በላይ ከፍታ ያላት ሲሆን ሜዳማ እና ተራራማ መልክዓ ምድራዊ ተፈጥሮ ተሸልማለች።

በሶስት ክፍለ ከተሞች እና በዘጠኝ ቀበሌዎች የተዋቀረችው ዲላ ከተማ የተለያዩ የሰፈር እና መንደር ስያሜዎችም አሏት፡፡ ከነዚህም ሁላ፣ ናገአ፣ ሻላዬ፣ ጎላ እና ዶምቦስኮ ይገኙበታል።

በአከባቢው በዓለም አቀፍ ደረጃ ተፈላጊ የሆነው ቡናን ጨምሮ እንሰት፣ ገብስና ስንዴ እንዲሁም ሌሎች ምርቶች ይመረታል፡፡ ዲላ በአትክልት እና ፍራፍሬ የምትታወቅ ሲሆን ማንጎ፣ ሙዝ፣ አቮካዶ እና ፖም ተጠቃሾች ናቸው።

ከከተማዋ ቅርብ ርቀት ላይ የሚገኙትን የቱቱፈላ ትክል-ድንጋይ እና ጥንታዊው የጪጩ ገብርኤል ገዳምን ጨምሮ የዋሻ ላይ ስዕሎች፣ ፏፏቴዎች እንዲሁም የፍል ውሃን ለመጎብኘት ለሚመጡ ቱርስቶች ምቹ ማረፊያና መዳረሻም ናት የድላ ከተማ።

ከተማዋ የጌዴኦ ዘመን መለወጫ በዓል የሆነው "ደራሮ" በድምቀት የሚከበርባትም ከተማ ናት።
👇👇
https://shorturl.at/tzCOT
#ከተሞቻችን
ጅግጅጋ

የምስራቋ ፈርጥ፣ የብዙኃን መናህሪያ እና የእንግዳ ተቀባይ ሕዝብ ምድር የሆነችው የጅግጅጋ ከተማ ከመዲናችን አዲስ አበባ በስተምስራቅ አቅጣጫ 618 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ትገኛለች፡፡

በአብዛኛው ሜዳማ ተፈጥሯዊ የመሬት ገፅታ የተጎናጸፈችው ይህች ከተማ የሶማሌ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ዋና መቀመጫ ናት፡፡

ከባህር ጠለል በላይ 1ሺሕ 609 ሜትር ከፍታ ላይ የምትገኘው ጅግጅጋ ሞቃታማ የአየር ንብረት አላት፡፡ ከተማዋ በ1916 ዓ.ም በፊታውራሪ ተክለ ሐዋሪያት ተክለ ማርያም እንደተመሰረተች ይነገራል።

ጅግጅጋ የሚለው ቃል መነሻው ሕዝቡ የውሃ ጉድጓዶች ሲቆፍር ከተሰሙ የተለያዩ የ"ጂግ-ጂግ" ድምፆች መሆኑ ይጠቀሳል፡፡ በአካባቢው ማኅበረሰብ "ላአ" ተብሎ ይጠራ እንደነበር እና ይህም በሶማሌ ቋንቋ "ማራኪ እይታ" ማለት እንደሆነ ይነገራል።

የካራማራ ሰንሰለታማ ተራራ ከጂግጂጋ ከተማ በ12 ኪ.ሜ ርቀት ላይ ይገኛል፡፡ ውብ እና አረንጓዴ መልከዓ ምድራዊ ተፈጥሮ ያለው ይህ ተራራ የካራማራ የድል ብስራት ህያው ምስክርም ጭምር ነው።

ጅግጅጋ በአራት ክፍለ ከተማ እና ሀያ ቀበሌዎች የተዋቀረች ስትሆን ክፍለ ከተማዎቿ ካራማርዳ፣ ዱዳሂዲ፣ ጋራብአሴ እና ቆርዴሬ ይባላሉ፡፡
👇👇
https://www.facebook.com/wmccwaltamediaandcommunicationcorporate/posts/pfbid02kXrPXbE7B9Zo2QiSZStaASibiaWH4tqHiUFMShGMcrqfnkZZ5YcUcwT7SffMBtP8l
ሆሣዕና
#ከተሞቻችን

ሆሣዕና ከማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ክላስተር ከተሞች አንዷ ስትሆን የሀዲያ ዞን አስተዳደር ዋና መቀመጫም ናት፡፡ ከተማዋ ከአዲስ አበባ በደቡብ አቅጣጫ 230 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ትገኛለች።

ሆሳዕና ከባህር ጠለል በላይ 2 ሺሕ 217 ሜትር ከፍታ ላይ የምትገኝና ወይናደጋ የአየር ንብረት ያላት ሜዳማ እና ተዳፋታማ ተፍጥሯዊ የመሬት ገፅታን ተላብሳለች፡፡

በ1888 ዓ.ም እንደተቆረቆረች የምነገርላት ሆሳዕና የከተማዋ የቀድሞ መጠሪያ ዋቸሞ እንደነበርና ወደ ሆሳዕና የቀየሩት ራስ አባተ ቧያለው ሲሆኑ ተሹምው ወደ ስፍራው ባመሩበት ዕለት እየተከበረ የነበረውን የሆሳዕና በዓል ምክንያት በማድረግ እንደሆነም ይነገራል።

ሆሣዕና በስድስት ቀበሌዎች የተዋቀረች ከተማ ስትሆን ኬንተሪ፣ ገብረፃዲቅ፣ የአብስራ፣ ማሪያም፣ ሞቢል፣ ቁጭራ፣ አራዳ እና ካናል/መሳለሚያ በሚል የሚጠሩ የሰፈር ስያሜዎችም አሏት።

በከተማዋ የከፍተኛ የትምህርት ተቋም የሆነውን ዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ ጨምሮ፣ ሆሣዕና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ፣ ሆሳዕና መምህራን ኮሌጅ እንዲሁም ቅድስት ስላሴ፣ ዋቸሞ 1ኛ ደረጃ፣ አለሙ ወልደሀና 2ኛ ደረጃ እና ሌሎችም ትምህርት ቤቶች ይገኛሉ።

ሆሣዕና ምቹ የሆቴል እና ቱሪዝም እንቅስቃሴ የሚታይባት ከተማ ስትሆን ቪክትሪ፣ አዲላ፣ ዋኣኔ መላይ፣ ዎዜ ስታር፣ በረከት እና የመሳሰሉ ደረጃቸውን የጠበቁ ሆቴሎች እና ሌሎች ይጠቀሳሉ።
👇👇
https://shorturl.at/ghpFR