AddisWalta - AW
45.1K subscribers
41.8K photos
204 videos
20 files
16.6K links
This is Walta Media and Communication Corporate’s official Telegram channel.

For more updates please visit https://shorturl.at/ehosX https://www.youtube.com/c/WaltaTV/featured
Download Telegram
ከንቲባ አዳነች አቤቤ የአንድ ወር ደሞዛቸውን ለ #ጽዱ_ኢትዮጵያ የዲጂታል ቴሌቶን ሰጡ

ሚያዚያ 20/2016 (አዲስ ዋልታ) የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ የአንድ ወር ደሞዛቸውን አስተዋፅኦ በማድረግ “ፅዱ ኢትዮጵያ” የዲጂታል ቴሌቶን ላይ መሳታፋቸውን አስታወቁ፡፡

ከከንቲባዋ ባሻገር የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አመራሮችም የ"ጽዱ ጎዳና -ኑሮ በጤና" ንቅናቄን ተቀላቅለዋል፡፡

በዚህም ጥሪውን በፍጥነት ሰለተቀላቀላቹ በከተማ አስተዳደር ስም ምስጋናዬን አቀርባለሁ ብለዋል፡፡

ያልተቀላቀሉ አመራሮችም ካምፔኑን እንዲቀላቀሉ በማኅበራዊ ትስስር ገፃቸው ጥሪ አስተላልፈዋል፡፡

በተጨማሪም ለአላማው መሳካት ሁሉም ሰው ያገባኛል በሚል በንግድ ባንክ በተከፈተው ሂሳብ ቁጥር 1000623230248 የ“ጽዱ ጎዳና - ኑሮ በጤና” ንቅናቄን እንዲቀላቀል ጥሪ አቅርበዋል::
ሰሜን ለንደን ደርቢ በአርሰናል የበላይነት ተጠናቀቀ

ሚያዝያ 20/ 2016 (አዲስ ዋልታ) በተጠባቂው የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ሰሜን ለንደን ደርቢ አርሰናል ቶተንሃምን 3 ለ 2 በሆነ ውጤት አሸንፏል፡፡

የአርሰናልን የማሸነፊያ ግቦች ሳካ፣ ሀቨርተስ እና ሆይቤር (በራሱ ግብ ላይ) አስቆጥረዋል፡፡

ቶተንሃምን ከሽንፈት ያላዳኑትን ግቦች ደግሞ ሮሜሮ እና ሰን አስቆጥረዋል፡፡

ውጤቱን ተከትሎም አርሰናል 80 ነጥቦችን በመያዝ በፕሪሚየር ሊጉ ደረጃ ሰንጠረዡ 1ኛ ላይ ሲቀመጥ ማንቼስተር ሲቲ ደግሞ ሁለት ተስተካካይ ጨዋታ እየቀረው በ76 ነጥብ ሁለተኛ ደረጃን ይዟል፡፡
ጠ/ሚ ዐቢይ አሕመድ ኬንያ ገቡ

ሚያዚያ 21/2016 (አዲስ ዋልታ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እና ልዑካን ቡድናቸው በዓለም አቀፉ የልማት ማኅበር (አይ ዲ ኤ) 21ኛ የማሟያ ጉባኤ ላይ ለመገኘት ናይሮቢ ኬንያ ገብተዋል።

ጉባኤው ማኅበሩ ደጋፊዎች እና ተባባሪ አካላት በአፍሪካ የልማት የገንዘብ ድጋፍ ቀዳሚ የትኩረት መስኮችን ለማመላከት እና አፅንዖት ለመስጠት ያለመ ሲሆን የገንዘብ ድጋፍ አቅራቢዎች በ21ኛው የማኅበሩ ዘመን ድጋፋቸውን ለመጨመር በፅኑ እንዲያጤኑ የማሳሰብ አላማ ያነገበም ነው።

ይህ ድጋፍ የአፍሪካን የልማት ተግዳሮቶች እና መልካም እድሎች በተገቢው መንገድ ለማስተናገድ እጅግ አስፈላጊ መሆኑን የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት መረጃ አመላክቷል።
የኢትዮጵያ በፈተናዎች ሁሉ የተሻገረ ያለመበገር ፅናት የምጣኔ ሀብት መረጋጋትን እና ምርታማነትን ባስቀደሙት በመዋቅራዊ የኢኮኖሚ ማሻሻያ ስራዎቿ ማሳያነት ይገለጣል - ጠ/ሚ ዐቢይ አሕመድ

ሚያዚያ 21/2016 (አዲስ ዋልታ) የኢትዮጵያ በፈተናዎች ሁሉ የተሻገረ ያለመበገር ፅናት የምጣኔ ሀብት መረጋጋትን እና ምርታማነትን ባስቀደሙት በመዋቅራዊ የኢኮኖሚ ማሻሻያ ስራዎቿ ማሳያነት ይገለጣል ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ።

በብሔራዊ የምክክር ኮሚሽን በሚመራው ስራ ምክክር እና እርቅ የሰላም ፍላጎታችን እና ተምኔታችን ማጠንጠኛ ናቸው ሲሉም ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው አስፍረዋል።

ትምህርትን ተደራሽ በማድረግ ብሎም ወጣቶችን በማብቃት ኢትዮጵያ ሁለት ሚሊዮን አዳዲስ ስራዎችን ለመፍጠር አልማለች ነው ያሉት።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ አረንጓዴ ዓሻራ በመሰሉ ንቅናቄዎች ኃይል ለሁሉም ማዳረስ፣ የዲጂታል ሽግግር እና የተፈጥሮ ከባቢን የመንከባከብ ተግባራትን ለመከወንም ትኩረት እንደምትሰጥ ገልጸዋል።

የዓለም አቀፍ የልማት ማኅበር ለአሕጉሩ ድጋፉን እንዲያጠናክር ኢትዮጵያ ጥሪ ታደርጋለች ብለዋል።
አዲስ ዋልታ ለመቄዶንያ የአልባሳት ድጋፍ አደረገ

ሚያዚያ 21/2016 (አዲስ ዋልታ) አዲስ ዋልታ ለመቄዶንያ በጎ አድራጎት ማኅበር የአልባሳት ድጋፍ አደረገ።

ተቋሙ ለመቄዶንያ ያደረገው ድጋፍ ለህፃናት እና አዋቂዎች የሚሆኑ የተለያዩ ዓይነት ልብሶችና ጫማዎችን ያካተተ ነው።

በድጋፍ የተበረከቱ አልባሳት ከዋልታ ሚዲያና ኮሙዩኒኬሽን ኮርፖሬት አመራሮችና ሠራተኞች የተሰበሰበ መሆኑም ተገልጿል።

ድጋፉ ከፊታችን በክርስትና እምነት ተከታዮች ዘንድ የሚከበረውን የትንሳኤ በዓልን ምክንያት በማድረግ የተደረገ እንደሆነም ተቋሙን ወክለው ድጋፉን ያበረከቱት ሰራተኞች አስታውቀዋል።

ተቋሙ ከዚህ በፊት በተለያዩ ጊዜ ለማዕከሉ የተለያዩ አይነት ድጋፎችን ማድረጉም ተመላክቷል።

መቄዶንያ የበጎ አድራጎት ማኅበር ጧሪና ደጋፊ የሌላቸውን በተለይም ራሳቸውን ችለው መንቀሳቀስ፣ መመገብ እና መፀዳዳት የማይችሉ አረጋዊያንንና አዕምሮ ሕሙማንን ከወደቁበት በማንሳት ከ7 ሺሕ 500 በላይ ተረጂዎችን በ25 ከተሞች እየረዳ ይገኛል።

ላለፉት 12 ዓመታት አገልግሎቱን በመስጠት ላይ የቆየው ማዕከሉ አገልግሎቱን ለማስፋት በ3 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር ወጪ ባለ 15 ወለል ሕንፃ እየገነባ ይገኛል።

በአድማሱ አራጋው
የ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ፈተና የሚሰጥበት ቀን ይፋ ሆነ

ሚያዚያ 21/2016 (አዲስ ዋልታ) የ2016 የትምህርት ዘመን የኢትዮጵያ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ማጠናቀቂያ ወይም የ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ፈተና የሚሰጥበት ቀን ይፋ ሆኗል።

የ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ፈተና ከሐምሌ 3 እስከ 5 ለማህበራዊ ሳይንስ እንዲሁም ከሐምሌ 9 እስከ 11/2016 ዓ.ም ለተፈጥሮ ሳይንስ ተፈታኞች በበይነ መረብ (ኦን ላይን) እና በዩኒቨርሲቲ ውስጥ በወረቀት ይሰጣል።

በወረቀት ላይ የሚፈተኑ የማህበራዊ ሳይንስ ተፈታኞች ሰኔ 30 እና ሐምሌ 01/2016 ዓ.ም እንዲሁም የተፈጥሮ ሳይንስ ሐምሌ 6 እና 7/2016 ዓ.ም ወደ ዩኒቨርስቲ እንደሚገቡ ከትምህርት ምዘናና ፈተናዎች አገልግሎት ያገኘነው መረጃ አመላክቷል።
ጠ/ሚ ዐቢይ አሕመድ ወደ ኬንያ ያመሩበትን ጉባኤ አጠናቀው ተመለሱ

ሚያዚያ 21/2016 (አዲስ ዋልታ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ወደ ኬንያ ያመሩበትን የአይ ዲ ኤ ጉባኤ አጠናቀው ወደ ኢትዮጵያ ተመልሰዋል።
ቄራዎች ድርጅት ግማሽ በግ ለበዓል ማቅረቡን አስታወቀ

• ኅብረተሰቡ ለበዓል እንደየአቅሙ እንዲገበያይ ስጋዎችን በተመጣጣኝ ዋጋ እንደሚያቀርብም ገልጿል

ሚያዝያ 22/2016 (አዲስ ዋልታ) የአዲስ አበባ ቄራዎች ድርጅት ኅብረተሰቡ ለበዓል እንደየአቅሙ እንዲገበያይ ስጋዎችን በተመጣጣኝ ዋጋ እንደሚያቀርብ ገለጸ።

ድርጅቱ ለ2016 ዓ.ም የፋሲካ በዓል ያደረገውን ዝግጅትን አስመልክቶ በሰጠው መግለጫ ሰው እንደአቅሙ እንዲገበያይ በማሰብ ግማሽ በግ መዘጋጀቱን ገልጿል።

በቄራ ከብት በኪሎ 570 ብር፣ ፍየል በኪሎ 510 ብር እና በግ በኪሎ 500 ብር ተጨማሪ እሴት ታክስን ጨምሮ እንደሚሸጥ የአዲስ አበባ ቄራዎች ድርጅት ማኔጂንግ ዳይሬክተር ሰኢድ እንድሪስ ተናግረዋል።

ለ2016 ዓ.ም የፋሲካ በዓል ከፍተኛ መጠን ያለውን እርድ ለማከናወን ዝግጅት መደረጉን ተናግረው በዚህም ከ7 ሺሕ 500 እስከ 8 ሺሕ እርድ ለማካሄድ መታቀዱን ገልጸዋል፡፡

ከግብዓት በተጨማሪ እስከ 250 ጊዜያዊ ሰራተኞች በመጨመር የአደረጃጀት ዝግጅት መደረጉንም ጠቁመዋል።

ተቋሙ ከሚመለታቸው አካላት ጋር በመተባበር 241 ህገወጥ ስጋ ይዘው የተገኙ ቤቶች ላይ እርምጃ መወሰዱን ገልጸው በዚህም 15 ሺሕ 295 ኪሎ ግራም ህገወጥ ስጋ ማስወገድ መቻሉን አብራርተዋል።

በቀጣይም ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመተባበር ህገወጥ እርድን በመከላከል የተጠናከረ እርምጃ እንዲሚወሰድና ለዚህም ህብረተሰቡ ህገወጥ እርድ በመጠቆምና በመከላከል የተመረመረና ጤናማ ስጋ እንዲመገብ አሳስበዋል።

በማህሌት መህዲ
ከመጸዳጃ ቤት እጥረትና ንጽሕናን ባለመጠበቅ የሚከሰቱ በሽታዎች

#ጽዱ_ጎዳና_ኑሮ_በጤና
ዲላ
#ከተሞቻችን

የአረንጓዴው ምድር የጌዴኦ ዞን አስተዳደር ከተማና የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የክላስተር ከተሞች አንዷ የሆነችው ዲላ ከመዲናችን አዲስ አበባ በደቡብ አቅጣጫ 365 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ትገኛለች፡፡

የፍቅር፣ የመተሳሰብ፣ የሰላም እና የአብሮነት ተምሳሌት የሆነችው ዲላ ከተማ በ1904 ዓ.ም ገደማ በቀድሞ የሲዳማ ሀገር ገዥ ባራምባራስ ደቻ ኡዶ እንደተቆረቆረች ይነገራል። ምስረታዋም ከቀረጥ ኬላ መከፈት ጋር ተያይዞ እንደሆነ መረጃዎች ይጠቁማሉ።

ቆላማ የአየር ንብረት ያላትና ነፋሻማዋ የዲላ ከተማ 1 ሺሕ 570 ሜትር ከባህር ጠለል በላይ ከፍታ ያላት ሲሆን ሜዳማ እና ተራራማ መልክዓ ምድራዊ ተፈጥሮ ተሸልማለች።

በሶስት ክፍለ ከተሞች እና በዘጠኝ ቀበሌዎች የተዋቀረችው ዲላ ከተማ የተለያዩ የሰፈር እና መንደር ስያሜዎችም አሏት፡፡ ከነዚህም ሁላ፣ ናገአ፣ ሻላዬ፣ ጎላ እና ዶምቦስኮ ይገኙበታል።

በአከባቢው በዓለም አቀፍ ደረጃ ተፈላጊ የሆነው ቡናን ጨምሮ እንሰት፣ ገብስና ስንዴ እንዲሁም ሌሎች ምርቶች ይመረታል፡፡ ዲላ በአትክልት እና ፍራፍሬ የምትታወቅ ሲሆን ማንጎ፣ ሙዝ፣ አቮካዶ እና ፖም ተጠቃሾች ናቸው።

ከከተማዋ ቅርብ ርቀት ላይ የሚገኙትን የቱቱፈላ ትክል-ድንጋይ እና ጥንታዊው የጪጩ ገብርኤል ገዳምን ጨምሮ የዋሻ ላይ ስዕሎች፣ ፏፏቴዎች እንዲሁም የፍል ውሃን ለመጎብኘት ለሚመጡ ቱርስቶች ምቹ ማረፊያና መዳረሻም ናት የድላ ከተማ።

ከተማዋ የጌዴኦ ዘመን መለወጫ በዓል የሆነው "ደራሮ" በድምቀት የሚከበርባትም ከተማ ናት።
👇👇
https://shorturl.at/tzCOT
ጠ/ሚ ዐቢይ አሕመድ የኮሪደር ልማት ስራ ሂደት ላይ ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አመራሮች ጋር ተወያዩ

ሚያዝያ 22/2016 (አዲስ ዋልታ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የኮሪደር ልማት ስራ ሂደት ምን ደረጃ ላይ እንዳለ ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አመራሮች እና የኮሪደር ልማት ስራ መሪዎች ጋር ተወያዩ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማኅበራዊ ትስስር ገፃቸው ከአንድ ወር በፊት የኮሪደር ልማት ስራ ሂደት ምን ደረጃ ላይ እንደሚገኝ አጠቃላይ ግምገማ ማድረጋቸውን አስታውሰዋል።

ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አመራሮች እና የኮሪደር ልማት ስራ መሪዎች ጋር በድጋሚ በመገናኘት በስራዎቹ እርምጃ ዙሪያ ጥልቀት ያለው ውይይት ማድረጋቸውንም ጠቅሰዋል።

እነኚህ ስራዎቻችን የግንባታ ብቻ ጉዳዮች አይደሉም፤ ይልቁንም ከተማችንን ወደ ላቀ ምቹ፣ ንቁ እና ዘላቂ የመኖሪያ ከባቢ የመለወጥ ጥረቶች ናቸው ብለዋል።

ሥነ-ውበትን በማሳደግ፣ አረንጓዴነትን በማስፋት ብሎም መሰረተ ልማትን በማሻሻል የህዝባችንን ጤና መጠበቅ ብቻ ሳይሆን የስራ ዕድሎችንም እየፈጠርን ነው ሲሉም አክለዋል።

በጋራ እነዚህ ጥረቶቻችን የአዲስ አበባን አጠቃላይ ይዞታ በማላቅ እውነትም ለሁሉም ነዋሪዎቿ ፍላጎቶች የተመቸች ያደርጓታል ነው ያሉት።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ መጪውን በዓል ምክንያት በማድረግ ዝቅተኛ ገቢ ላላቸው የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ሠራተኞች እና ጽሕፈት ቤቱ ለሚያሳድጋቸው አሳዳጊ የሌላቸው ሕጻናት ማዕድ አጋርተዋል።
በከንቲባ አዳነች አቤቤ የተመራው ልዑክ የኢትዮጵያ አየር ኃይልን ጎበኘ

ሚያዚያ 23/2016 (አዲስ ዋልታ) በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ የተመራው የአስተዳደሩ የስራ ኃላፊዎች ቡድን በኢትዮጵያ አየር ኃይል ጉብኝት አደረገ።

በጉብኝቱ ላይ ከንቲባ አዳነች አቤቤ እንደተናገሩት አየር ኃይላችን በላቀ የስራ ትጋትና ጥራት ያለንን ሀብት ተጠቅሞ ለውጥ ማምጣት እንደሚቻል አንዱ ማሳያ የሆነ ተቋም ነው ብለዋል፡፡

በሰላም እንዲሁም እንደ ሀገር ለተያዘው የልማት ጉዞ መከላከያችን ያፀናው ሰላም ወሳኝ መሆኑን ያስታወቁት ከንቲባ አዳነች የኢትዮጵያ አየር ኃይል ለመላው ኢትዮጵያዊያን የኩራት ምንጭ የሆነ ታላቅ ተቋም መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ እና የኢንዱስትሪ ቢሮ ኃላፊ ጃንጥራር አባይ በበኩላቸው የኢትዮጵያ አየር ኃይል ለሀገር አንቱታን ያተረፈ ትልቅ ተቋም መሆኑን አውስተው የግዛት አንድነታችን እንዲሁም ሉዓላዊነታችንን በማስጠበቅ አንጋፋው የአቭዬሽን ተቋም መሆኑን ጠቁመዋል።

የኢፌዴሪ አየር ኃይል ዋና አዛዥ ሌተናል ጄኔራል ይልማ መርዳሳ በበኩላቸው በሀገራችን የተጀመረው ተቋማትን ውብ እና ፅዱ አድርጎ የመገንባቱ ተግባር በአየር ኃይል ይበልጥ ተጠናክሮ መቀጠሉን ገልፀዋል፡፡

ከንቲባዋና ካቢኔያቸው በተቋሙ ያደረጉት ጉብኝት ትልቅ ፋይዳ ያለው የሞራል ስንቅ ነው ማለታቸውንም ከከንቲባ ፅህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

በዕለቱ በአየር ኃይል መምሪያ ግቢ ውስጥ እየተከናወኑ ያሉ የግብርናውን ልማት እና ሌሎች ከለውጡ ወዲህ የተሰሩ መሰረተ ልማቶችን ከንቲባዋና ካቢኔያቸው ተዘዋውረው ጎብኝተዋል፡፡
የጠ/ሚ ጽሕፈት ቤት የ‘ገበታ ለሀገር' ፕሮጀክቶችን ለክልሎች አስረከበ

ሚያዚያ 24/2016 (አዲስ ዋልታ) የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት የ‘ገበታ ለሀገር' ፕሮጀክቶችን ለአማራ፣ ለኦሮሚያ እና ለደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት አስረክቧል።

በተጨማሪም በገበታ ለሀገር የተገነቡ ሎጆችን ስራ የማስኬድ ተግባርን የኢትዮጵያ አየር መንገድ በስካይ ላይት ሆቴል ተቋሙ በኩል እንዲወጣ የስምምነት ፊርማ ሥነ ሥርዓት ተካሂዷል።

ከአራቱ የገበታ ለሀገር ፕሮጀክቶች ሶስቱ (ሃላላ ኬላ ሎጅ፣ ጨበራ ጩርጩራ የዝሆን ዳና ሎጅ እና ወንጪ ኢኮ ሎጅ) በቅርቡ መመረቃቸው የሚታወሰ ሲሆን የጎርጎራ ፕሮጀክት ስራም በመጠናቀቅ ላይ ይገኛል።

በጠቅላይ ሚኒስሩ ከፍተኛ ትኩረት እና አመራር የተከናወነው የ’ገበታ ለሀገር’ ስራ የብሔራዊው የሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ አንዱ ማዕዘን የሆነውን ቱሪዝምን የማሳደግ አላማ ያለው ነው።

እነዚህ ፕሮጀክቶች በመጀመሪያው ፋይናንስ የማሰባሰብ ምዕራፍ የኅብረተሰቡን ድጋፍ በሰፊው ያሰባሰቡ፣ በግንባታቸው ምዕራፍ ግዙፍ የስራ ዕድል የፈጠሩ ብሎም ታላላቅ የመሰረተ ልማት ስራዎች እንዲከናወን በር የከፈቱ ናቸው።

በፈጠራ የተሞላ የፕሮጀክት ስራ እና አስተዳደር እና ፈጣን አፈፃፀም ምን ሊመስል እንደሚችል ማሳያም መሆናቸውን የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት አመላክቷል።

ቀጣይ የስራ ማስኬድ እና ማስተዳደር ተግባሩ ለብሔራዊ ሰንደቅ ተሸካሚው የኢትዮጵያ አየር መንገድ በሃላፊነት መሰጠቱም የተሻለ አገልግሎት እንዲሰጥ ከማስቻሉም ባለፈ ለዓለም አቀፍ የቱሪዝም መዳረሻነት ትውውቅ ከፍ ያለ ዕድል ይፈጥራል ተብሏል።