ውሉደ ብርሀን ሰ/ት/ቤ/ት🙏(ጫንጮ)
766 subscribers
84 photos
4 files
98 links
ሰንበት ትምህርት ቤት የመልካም ወጣት የመልካም ትውልድ መፍለቂያ ናት! ትውልድን ለበጎ ነገር የምታበቃ ናት፡፡


የጫንጮ ከተማ ደ/ብ/ቅ/እግዚአብሔር አብ እና ደ/ሲ/ቅ/ ኪዳነ ምህረት ቤ/ክ ው/ብ/ሰ/ት/ቤት ቻናል
ለሀሳብ እና አስታየት @weldebirhanbot @ty1921 ይጠቀሙ

ወንድሞች በህብረት ቢቀመጡ መልካም ነው፡፡
Download Telegram
ከጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ልደት ያገኘነው ምንድን ነው?
#ዳግም_ልደት
በአዳም በደል ምክንያት አጥተነው የነበረው ልጅነታችንን ክርስቶስ በልደቱ ዳግመኛ እንደመለሰልን ነባቤ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስ “ለተቀበሉት ሁሉ ግን በስሙ ለሚያምኑት ለእነርሱ የእግዚአብሔር ልጆች ይሆኑ ዘንድ ሥልጣንን ሰጣቸው።” ዮሐ 1፥12 በማለት ገልጾታል።
#ሰላም
በጌታችን ልደት ለዓለም ሁሉ የሚሆን ዘላለማዊ ሰላም ተገኝቷል። ይህም “ክብር እግዚአብሔር በሰማያት ይሁን ሰላምም በምድር ለሰውም በጐ ፈቃድ” እያሉ ቅዱሳን መላእክት በመዘመራቸው ተረጋግጧል። ሉቃ 2፥14። ስለዚህ በክርስቶስ ያገኘነው እውነተኛ ሰላም በእኛ ጸንቶ እንዲኖር ዘወትር በጾምና በጸሎት እየተጋን ስለሰላም የምንማፀን ሆነን ልንገኝ ይገባል። ሰላም የክርስትና መታወቂያ አርማ ነውና።
#ብርሃን
“በጨለማ የሄደ ሕዝብ ብርሃንን አየ፤ በሞት ጥላ አገርም ለኖሩ ብርሃን ወጣላቸው።” ኢሳ 9፥2። ለአምስት ሺህ አምስት መቶ ዘመን ያህል በዲያብሎስ ቁራኝነት ተይዞ የነበረው አዳም ወደሚደነቀው ብርሃን የተሸጋገረው በክርስቶስ ልደት ነው። እኛም በልደቱ ያገኘነውን የጽድቅ ብርሃን ጠብቀን ለመኖር (ብርሃነ ወንጌልን) ፈጽመን ከኃጢአት ርቀን በጽድቅ ሥራ ተወስነን ብርሃን ሆነን ልንኖር ይገባል።
#ነጻነት
“በነጻነት እንኖር ዘንድ ክርስቶስ ነጻ አወጣን። ከእንግዲህ ጸንታችሁ ቁሙ እንደገና በባርነት ቀንበር አትያዙ”። ገላ 5፥1። የሰው ልጅ እግዚአብሔርን በነጻነት እያመሰገነ ይኖር ዘንድ ተፈጥሯልና። ኃጢአት በመሥራት የዲያብሎስ ባርያ ሳንሆን በተሰጠን ነጻነት በመጠቀም የጽድቅ አገልጋዮች ሆነን ልንመላለስ ይገባል።
#ይቅርታ
በአዳም በደል ምክንያት ከአብራኩ የተከፈሉ በሙሉ በደለኛ ሆነው የነበሩበትን ዘመን ለውጦ አዳምንና የልጅ ልጆቹን በደል ደምስሶ ፍቅርን ይመሰርት ዘንድ ጌታ ተወለደ። በምድርና በሰማይ ላሉት ፍቅርን መሠረተ። እርሱ የሰው ልጆችን በደል ሳይቆጥር ሁሉን ይቅር እንዳለ ክርስቲያንም የበደሉትን ሁሉ ይቅር ይል ዘንድ የፈጣሪው ትዕዛዝ ነውና ዘወትር ሊፈጽማት የምትገባ ከእግዚአብሔር ጸጋ የምታስደምር የልደቱን ብርሃን ለማየት እንደበቁ በዚህም ደስ እንደተሰኙ እንደ ቅዱሳን መላእክት ለእውነተኛ ምስጋና የምታደርስ የጽድቅ መሠረት የበረከት በር ናት። ማቴ 18፥21-23፣ ማቴ 5፥23-25። መባህን ትተህ ሂድ አስቀድመህም ከወንድምህ ጋር ታረቅ በኋላም መጥተህ መባህን አቅርብ የሚለው አምላካዊ ቃል ይቅርታ የክርስትና ሕይወት መመሪያ መሆኑን ያሳያልና ዘወትር ልንፈጽማት ይገባል።
#ፍቅር
ፍቅር ሰሃቦ ለወልድ ኃያል እም መንበሩ ወአብጽሖ እስከለሞት /ፍቅር ኃያል ወልድን ከዙፋኑ አወረደው እስከ ሞትም አደረሰው።/ ሊቁ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ እንደተናገረው እግዚአብሔር አምላክ የሰው ልጅን በደል ሳይቆጥር በዙፋኑ ሆኖ ምሬሃለሁ ማለት ሲችል ፍቅሩን ይገለጽ ዘንድ በከብቶች በረት ተወለደ። እውነተኛ ፍቅሩ ለክርስትናችን መሠረት ለጽድቃችን ፋና እንደሆነ መጻሕፍት ያረጋግጣሉ።
እንግዲህ በልደቱ ያገኘነውን ሰላም፣ ነጻነት፣ ይቅርታ፣ ብርሃንና ፍቅር ዋጋ የተከፈለበት ጸጋ የወረስንበት በመሆኑ ዘወትር በድንቅ ፍቅሩ የሚታደገን አምላካችን እግዚአብሔር በሰጠን ጸጋ እስከ መጨረሻው ድረስ ጸንተን እንድንኖር ክብራችንንና ጸጋችንን አስተውለን ከኃጢአት ርቀን በንሰሐ ታጥበን እራሳችንን ለክርስቶስ የተወደደ መስዋዕት አድርገን እንድናቀርብ የእግዚአብሔር ቸርነት የድንግል ማርያም አማላጅነት የቅዱሳን መላእክት ተራዳኢነት አይለየን።
አሜን

🙏🙏🙏🙏ይህንን ያውቃሉ🙏🙏🙏🙏🙏🙏🙏🙏🙏🙏🙏🙏🙏🙏🙏🙏🙏🙏🙏
🌹🌹🌹🌹🌹🌹🌹🌹🌹🌹🌹🌹🌹
❖ ❖ ❖እነሆ ዛሬ በዳዊት ከተማ መድኀኒት ተወልዶላችኋል ሉቃ.2፥11 ❖ ❖ ❖
❖ ❖ ❖ እንኳን ለጌታችን ለመድኀኒታችን ለኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓል በሰላም አደረሳችሁ፡፡ ❖ ❖ ❖
🌹🌹🌹🌹🌹🌹🌹🌹🌹🌹🌹🌹🌹

❖ ❖ ❖ " ጌና" ❖ ❖ ❖
ጌና እና ልደት {ዋዜማና ክብረ በዓል }
/የተለያዩ ቀናት/ ቢኾኑም ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ግን ጌና ልደትን እየተካ እንጠቀምበታለን ፤ ነገር ግን ይህ ሊስተካከል ይገባዋል፡፡ ልዩነት ስላለውም የኢትዮጵያ ብርሃን የተባለው አፈ ጳዝዮን አባ ጊዮርጊስ ዘጋሥጫ ለጌናና ለልደት ለ2ቱም በዓላት ለየብቻቸው በመጽሐፈ ምሥጢር ድርሰት ደርሶላቸዋል፡፡
#ጌና ፤ የልደት በዓል ዋዜማ ቀን ሲኾን በዚህ ቀን ‹‹በገና ጨዋታ አይቆጡም ጌታ›› የተባለለትን ‹‹የገና ጨዋታ›› እንጫወታለን፤ የምንጫወትበት የኳሱ ስያሜ ‹‹ሩር›› ሲባል ስያሜውን ያገኘው፤ ሰብዓ ሰገል እልፍ እልፍ ሠራዊት አስከትለው የተወለደውን የአይሁድ ንጉሥ ፍለጋ ወደ ንጉሡ ሔሮድስ ደርሰው ነበርና ፤ ሔሮድስ ሕፃኑን ሊገድለው ፈልጎና በውስጡ ሸሽጎ ለሰብዓ ሰገል ሂዱ ሕፃኑን ፈልጉ ስታገኙትም ንገሩኝ ብሎ ሰድዷቸዋል ፤ ነገር ግን በዚያው ሳይነግሩኝ እንዳይሄዱ በማለት እነርሱ ሳያውቁ ‹‹ሩር›› የተባለ ሰላይ በመሃላቸው አስገብቶ ነበርና ሰብዓ ሰገልን ይመራቸው የነበረው ኰከብ ተሠውሮባቸዋል ፤ ሰብዓ ሰገል ሠራዊታቸውን ቢያጣሩ ከመሃከላቸው የተቀላቀለ ሩር የተባለ የሔሮድስን ሰላይ አገኙ ይህንንም ሰላይ የሰብዓ ሰገል ሠራዊት አንገቱን በሰይፍ ቀልተውታልና ያን ለማስታወስ ዛሬ በገና ጨዋታ ላይ ሩር የተባለው ኳስ የሔሮድስ ሰላይን ‹‹ሩር›› እንዲያስታውስ አባቶች ሥርዐትን ሠሩ፡፡

❖ ❖ ❖ የጌታችን የመድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓል ❖ ❖ ❖
የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ልደት እንደ እንግዳ ደራሽ እንደ ውኃ ፈሳሽ አይደለም፡፡ ከጥንት ከመሠረት ጀምሮ በመላእክት ፤ በነቢያት ሲነገር ፤ ሲሰበክ የመጣ ነው እንጂ፡፡ ማቴ.1፥18፡፡ ሰው የመሆኑን ምሥጢር ለመጀመሪያ ጊዜ በማዕከለ ገነት የተናገረ እርሱ እግዚአብሔር ነው፡፡
አባታችን አዳም ከእግዚአብሔር ትዕዛዝ ወጥቶ ዕፀ በለስን በልቶ ከጸጋ እግዚአብሔር በተራቆተ ጊዜ /አዳም ኮነ ከመ አሐዱ እምኔነ/ አዳም ከእኛ እንደ አንዱ ሆነ ዘፍ.3፥22 ብሎ ከሦስቱ ቅዱስ አንዱ ቅዱስ እግዚአብሔር ወልድ በተለየ አካሉ ከእመቤታችን ከሥጋዋ ሥጋ ከነፍሷ ነፍስ ነስቶ ሰው እንደሚሆን ተናግሯል፡፡ በዚህ ቃል መሠረት /መሪነት/ ቅዱሳን መላእክት ምሥጢረ ትንቢት ተገልጾላቸዋል፡፡ እነሱም የተገለጸላቸውን ምሥጢረ ትንቢት ኀላፍያትንና መጻእያትን ለሚናገሩ ነቢያት ነግረዋቸዋል፡፡ ቅዱሳን ነቢያትም ከእግዚአብሔር ያገኙትን ከመላእክት የሰሙትን መነሻ አድርገው በተለያዩ ጊዜያት በተለያዩ ምሳሌያት በተለያዩ ዘመናት የወልደ እግዚአብሔርን ሥጋዌ ሰብከዋል /ገልጸዋል/ ዕብ.1፥1፡፡ ከጥንት ጀምሮ እግዚአብሔር በብዙ ዓይነትና በብዙ ጎዳና ለአባቶቻችን በነቢያት ተናግሮ ፥ ሁሉን ወራሽ ባደረገው ደግሞም ዓለማትን በፈጠረበት በልጁ በዚህ ዘመን መጨረሻ ለእኛ ተናገረን፡፡

የጌታችን ልደት በትንቢተ ነቢያት ፦
👉 ከዓበይት ነቢያት መካከል አንዱ የሆነው ነቢየ እግዚአብሔር ኢሳይያስ የሚከተለውን ትንቢት ተናግሯል፡፡
"እነሆ ድንግል በድንግልና ፀንሳ በድንግልና ትወልዳለች ስሙንም አማኑኤል ትለዋለች ( ኢሳ.7፥14፣ ሕዝ.44፥1) ፡፡ በኅቱም ድንግልና ተፀንሶ በኅቱም ድንግልና የተወልደው አማኑኤል ጌታ ነው፡፡ ትርጉሙም እግዚአብሔር ከእኛ ጋር ሆነ ማለት ነው፡፡ነቢዩ በጎላና በተረዳ ነገር “ሕፃን ተወልዶልናል ወልድ ልጅም ተሰጥቶናል አለቅነትም በጫንቃው ላይ ይሆናል፡ ስሙም ድን
#_ግንቦት_26_ለዓለም ብርሃን የሆኑ  #ኢትዮጵያዊው_ጻድቅ_አቡነ_ሀብተ_ማርያም_ልደታቸው_ነው፡፡

በመብረቅ፣ በቸነፈር፣ በረሃብ፣ በወረርሽኝ፣ በእሳት ቃጠሎ ላይ ቃል ኪዳን የተሰጣቸውን የእኒህን ጻድቅ #ታሪካቸውን_መልክአቸውና_በ ቃሌ ተራራ ደብረ መድኀኒት አቡነ ሀብተማርያም ገዳም( አዲስ አበባ ከዊንጌት ትምህርት ቤት አካባቢ) የሚቆመውን ሥርዓተ ማኀሌት እንሆ ብለናል፡፡
                          #share
አቡነ ሀብተማርያም
፠፠በማዕጠንታቸው የታወቁ፤
፠፠በጽድቅ ሥራቸው የተደነቁ፤
፠፠5ት መቅሰፍቶችን የሚያርቁ ታለቅ አባታችን ናቸው፡፡፡፨

፠በመራ ውዕይ (ሸዋ ፥ ቡልጋ) ከአባታቸው #ፍሬ ቡሩክና ከእናታቸው ቅድስት #ዮስቴና ነው የተወለዱት፡፡ ወላጆቹ በተለይም እናቱ ከማግባቷ በፊት መንና ነበር፡፡ ጻድቁን እንደምትወልድ በበቃ ባሕታዊ ተነግሯት ጻድቁን ወልዳ በጽድቅ ኑሮ ኑራ #7_አክሊላትን ተቀብላ በክብር አርፋለች፡፡

፠አቡነ ሀብተማርያም በሕፃንነታቸው ከእናታቸው ጋር ቆመው ሲያስቀድሱ ‹‹እግዚኦ መሐረነ ክርስቶስ›› ሲባል ይሰማሉ፤ በሕፃን አንደበታቸው ይዘው ሌሊት ሌሊት እየተነሱ ‹‹ማረን እባክህን›› እያሉ ይሰግዱ ነበር፡፡ ትንሽ ከፍ ብለው በእረኝነት ሳሉም ፍጹም ተሐራሚና ጸዋሚ ነበሩ፡፡ ጸጋው ስለ በዛላቸውም ልጅ ሆነው ብዙ ተአምራትን ሠርተዋል፤ ጓደኞቻቸው የሌላ ሰው እሸት እየነቀሉ ሲበሉ እርሳቸው ግን አይበሉም ነበር፡፡ የፈጣሪውን ስም ያቃለለውን አንድ እረኛም በአየር ላይ ሰቅለው አውለውታል፡፡

፠ወደ ት/ቤት ገብተው ትምህርትን ከቀሰሙ በኋላ ለአካለ መጠን ሲደርሱ ቤተ ሰቦቻቸው ሚስት አጩለት፤ እርሱ ግን ወደ አፋር ከአባ ሳሙኤል ዘንድ ሂዶ ለ12 ዓመታት ረድዕ ሆኖ ተቀመጠ፡፡ ከአፋርም ወደ ምኔት ወደሚባል ቦታ መጥቶ በታላቁ አባት በአባ መልከ ጼዴቅ እጅ መነኰሰ፤ ከአፋር ወደ ይነውፋ፥ ከይነውፋ ወደ ጉሐርብ ወደሚባል ሃገር ሂዶ ምናኔን፣ ትሩፋትንና ተጋድሎን ሠራ፡፡
ለአብነትም፤
ባሕር ውስጥ ሰጥሞ 500 ጊዜ ይሰግዳል፤
በየቀኑ 4ቱን ወንጌልንና 150 መዝሙረ ዳዊትን ይጸልያል፤
በ40 ቀናት ቀጥሎም በ80 ቀን አንዴ ብቻ ይመገባል፤
ምግቡ ደግሞ ሣርና ቅጠል ብቻ ነው፤
በየዕለቱ ያለ ማስታጐል ማዕጠንት ያሳርጋል፤
ዘወትር በንጽሕና ቅዱስ ሥጋውን ይበላል፥ ክቡር ደሙን ይጠጣል፤
በልቡ ውስጥ በፍጹም ቂምን፣ መከፋትን አያሳድርም፡፡
የብረት ሰንሰለት በወገቡ ታጥቆ ይሰግዳል ይጸልያልም፡፡
"ጽድቅና ትሩፋት እንደ ሀብተ ማርያም"  የተባለላቸው ታላቅ አባታችን ናቸው   ፡፡

፠ዲቁናን ከጳጳሱ አቡነ ይስሐቅ ዘንድ ተቀበሎ ወደ በዓቱ ተመለሰ፡፡
፠ኋላ ቆይቶም እንደገና ከአቡነ ይስሐቅ ዘንድ ቅስናን ተቀበለ፡፡ ወደ ጓና ወደ ምትባል ሀገርም ሂዶ ተቀመጠ፡፡ ቀጥሎም ጐላጐት ወደ ምትባል አገር ሂዶ ተቀመጠ፡፡
*የአፄ ናዖድ የንስሐ አባት ነበረና ንጉሡን ያስተምረውና ይገስጸውም ነበር፡፡
፠ጌታችንም ለጻድቁ የእሳትና የብርሃን ሠረገላን ሰጥቶት በዚያ እየበረረ ወደ ኢየሩሳሌምና ወደ ተለያዩ ቦታዎች ይሔድ ነበር፡፡ ከብዙ የተጋድሎ ዘመናት በኋላም የክብር ባለቤት መድኀኒታችን ክርስቶስ አእላፍ መላእክትን አስከተትሎ መጥቶ እንዲህ አላቸው::

"*ስለ እኔ ረሃብና ጥምን ስለ ታገስክ: *ስለ ምናኔሕ: *ስለ ተባረከ ምንኩስናህ: *ስለ ንጹሕ ድንግልናህ: *ቂምና በቀልን ስላለመያዝህ: *ስለ ንጹሕ ክህነትህና ማዕጠንትህ: *ቅዱስ ወንጌልን በፍቅር ስለ ማንበብህ 7 አክሊላትን እሰጥሃለሁ::"

"በሰማይም ከመጥምቁ ዮሐንስ ጐን: 500 የዕንቊ ምሰሶዎች ያሉበትን አዳራሽ ሰጥቼሃለሁ:: በስምህ የሚለምኑ: በቃል ኪዳንህ የሚማጸኑትንም ሁሉ እንድምርልህ 'አማንየ በርእስየ' ብዬሃለሁ" አላቸው::

+ቅዱሳን መላእክትም "ሀብተ ማርያም ወንድማችን" ሲሉ አቀፏቸው:: ጌታ ግን በዚያች ሰዓት አንድም ሦስትም ሆኖ ታያቸውና አቅፎ 3 ጊዜ ሳማቸው:: ከፍቅሩ ጽናትም የተነሳ ነፍሳቸው ከሥጋቸው ተለየች:: መላእክትም ዝማሬም ወሰዷት::

 ከተሰጣቸው ቃል ኪዳኖች ውስጥ አምስት መቅሰፍቶች የማስወገድ ሥልጣን ተሰጧቸዋል፡፡ እነርሱም፤
፩ኛ. #መብረቅ
፪ኛ. #ቸነፈር
፫ኛ. #ረሃብ
፬ኛ. #ወረርሽኝ
፭ኛ. #የእሳት ቃጠሎ ናቸው፡፡

፨በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ትዕዛዝ ቦታውን ሲባርክ ሦስት አጋንንት በጸሎቱ ሥልጣን የታሠሩለት ታላቅ ጻድቅ ነው፡፡
በግንቦት 26 ተወልዶ፤ በ1490 ዓ.ም. በወርኀ ኅዳር 26 ባረፈ ጊዜም፤ ካህናት በመልካም ልብስ ገንዘው በዝማሬ በማኅሌት ከቅዱስ አባታችን ከአቡነ ተክለሃይማኖት አጽም ጋር በደብረ ሊባኖስ ቀበሩት፡፡
(ከወርቅ ንፁህ ከብርም የጠራ ከሁሉ የሚበልጥ የተመረጠ ሃብተማርያም መልአክ ዘበምድር ነው መልካሙ ዜናው እስከ አጽናፍ ተሰማ፡፡)

ክብርት በሆነችው ጸሎቱና ምልጃው ይማርን ይጠብቀን፡፡

#ሰላም_ለጽንሰትከ_እማኅፀነ_ቅድስት_ዮስቴና
#በብሥራተ_ጻድቅ_ባሕታዊ_ሠናየ_ዜና፡፡
#ሀብተማርያም_ጴጥሮስ_ሐዋርያ_ወልደ_ዮና
#መሐረኒ_ምግባረ_ጽድቅ_ወጸግወኒ_ልቡና
#አፍቅሮ_ቢጽ_እኅሥሥ_ዘምስለ_ፍጽመት_ትሕትና፡፡
https://t.me/yeberhanljoche
​​​​እንኳን ለታላቁ ነቢይና ሰማዕት ቅዱስ ዮሐንስ መጥምቅ ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ

#ቅዱስ_ዮሐንስ_መጥምቅ

ቅዱስ ወንጌል ላይ ከእመቤታችን ቀጥሎ የነ ዘካርያስን ቤተሰብ ያህል ክብሩ6 የተገለጠለት ፍጡር ይኖራል ብሎ መናገሩ ይከብዳል:: #ቅዱስ_ሉቃስ ወንጌሉን የጀመረው በዚህ ቅዱስ ቤተሰብ ነውና መንፈስ ቅዱስ እንዲህ ሲል አጽፎታል:: "#ዘካርያስ ካህኑና #ቅድስት_ኤልሳቤጥ በሰውና በእግዚአብሔር ፊት ያለ ነቀፋ የሚኖሩ ጻድቃን ነበሩ" ይላቸዋል:: (ሉቃ. 1:6)

¤የሰውን እንተወውና በእግዚአብሔር ፊት ያለ ነቀፋ መኖር ምን ይረቅ? ለዚህ አንክሮ (አድናቆት) ይገባል!

¤እሊህ ቅዱሳን ባልና ሚስት ግን መካኖች በመሆናቸው ልጅ ሳይወልዱ ዘመናቸው አልፎ ነበር:: እንደ ቤተ ክርስቲያን ትውፊት ዕድሜአቸው የኤልሳቤጥ 90 የዘካርያስ 100 ደግሞ ደርሶ ነበር::

¤ፍጹም መታገሳቸውን የተመለከተ ጌታ ግን በስተ እርጅናቸው ከሰው ሁሉ በላይ የሆነ: ትንቢት ለብቻው የተነገረለት (ኢሳ. 40:3, ሚል. 3:1) ታላቅ ነቢይን ይሰጣቸው ዘንድ መልአከ ብሥራት ቅዱስ ገብርኤልን ላከላቸው::

¤ቅዱስ ዘካርያስ ሰው ነውና ከደስታ ብዛት በመከራከሩ ድዳ ሆነ:: ቅድስቲቷ ግን መስከረም 26 ቀን ታላቁን ሰው ጸንሳ ለ6 ወራት ራሷን ሠወረች:: በ6ኛው ወር የፍጥረት ሁሉ ጌታ በተጸነሰ ጊዜ የአርያም ንግሥት ድንግል #እመቤታችን ደጋ ደጋውን ወደ ኤልሳቤጥ መጣች:: ሁለቱ ቅዱሳት የእህትማማች ልጆች ናቸው::

¤የአምላክ እናቱ ስትደርስና "#ሰላም" ስትላቸው መንፈስ ቅዱስ በእናትና ልጅ ወርዶ ኤልሳቤጥ በምስጋና: ዮሐንስ ደግሞ ገና በማሕጸን ሳለ በደስታ ዘለለ (ሰገደ):: ከዚህ በሁዋላ ሰኔ 30 ተወልዶ: አባቱ ዘካርያስ "ዮሐንስ" ሲለው አንደበቱ ተፈትቶለታል::

¤ቅዱስ ዮሐንስ ከተወለደ 2 ዓመት ከ6 ወር በሆነው ጊዜ #ሰብአ_ሰገል በመምጣታቸው በእሥራኤል ምድር የሚገኙ ሕጻናትን ሔሮድስ ቁዝ አስፈጀ:: ትንሽ ቆይቶም አይሁድ ለሔሮድስ ስለ ቅዱሱ ሕጻን ነገሩት:: "ሲጸነስ የአባቱን አንደበት የዘጋ: ሲወለድ ደግሞ የከፈተ 'ዮሐንስ' የሚባል ሕጻን አለና እሱንም ግደል" አሉ::

¤እናቱ ቅድስት ኤልሳቤጥ ይዛው ስትሸሽ ካህኑን ዘካርያስን ግን በቤተ መቅደስ መካከል ገድለውታል:: አረጋይት ኤልሳቤጥም ሕጻኑን እያሳደገች በገዳመ ዚፋታ ለ3 (5) ዓመታት ቆይታለች:: ቅዱስ ዮሐንስ 5 (7) ዓመት ሲሞላው ግን እዚያው በበርሃ እናቱ ዐረፈች:: ከሰማይ ዘካርያስና #ስምዖን ወርደው ቀበሯት::

¤ሕጻኑ ዮሐንስ ሲያለቅስ #ድንግል_ማርያም ስንት አገር አልፋ ሰማችው:: እርሷም ስደት ላይ ነበረችና:: ከጌታ ጋር በደመና ሒደው ድንግል አቅፋ አጽናናችው:: ጌታንም "እንውሰደው ይሆን?" አለችው:: ጌታችን ግን "ለአገልግሎት እስክጠራው እዚህ ይቆይ" አላት:: ባርካው: አጽናንታውም ተለያዩ::

¤ቅዱስ ዮሐንስ ከዚህ በሁዋላ በዚያ ቆላ የግመል ጠጉር ለብሶ: ጠፍር ታጥቆ ተባሕትዎውን ቀጠለ:: ለ25 (23) ዓመታትም በንጽሕና ሲኖር ከምድር አራዊትና ከሰማይ መላእክት በቀር ማንንም አላየም:: ይሕችን ዐመጸኛ ዓለምም አልቀመሳትም::

¤ከዚህ በሁዋላ 30 ዘመን ሲሞላው እግዚአብሔር ከሰማይ ተናገረው:: "ሒድ! የልጀን ጐዳና ጥረግ" አለው:: ነቢያት ስለዚህ ነገር ተናግረው ነበርና:: (ኢሳ. 40:3, ሚል. 3:1) አባቱ ዘካርያስም "ወአንተኒ ሕጻን ነቢየ ልዑል ትሰመይ: እስመ ተሐውር ቅድመ እግዚአብሔር ከመ ትጺሕ ፍኖቶ" (ሉቃ. 1:76) ብሎ መንገድ ጠራጊነቱን ተናግሮ ነበርና::

¤ቅዱስ ዮሐንስ በዚያ ጊዜ በኃይለ #መንፈስ_ቅዱስ እየገሰገሰ ከበርሃ ወደ ይሁዳ መጣ:: ያዩት ሁሉ ፈሩት: አከበሩት:: ቁመቱ ቀጥ ያለ: ጽሕሙ እንደ ተፈተለ ሐር የወረደ: ጸጉሩ የቁራ ያህል የጠቆረ: መልኩ የተሟላ: ግርማው የሚያስፈራ ገዳማዊ ነውና::

¤ፈጥኖም ሕዝቡን ለንስሃ ሰበከ:: ለንስሃም በርካቶችን አጠመቃቸው:: በዚህ አገልግሎት ለ6 ወራት ቆይቶ ጌታችን ወደ እርሱ ዘንድ መጣ:: ዮሐንስ ሰማይን ከነግሱ: ምድርን ከነ ልብሱ የያዘ ፈጣሪ 'አጥምቀኝ' ብሎ ሲመጣ ደነገጠ:: የሚገባበትም ጠፋው::

¤"እንቢ ጌታየ! አንተ አጥምቀኝ" አለው:: ጌታ ግን "ፈቅጄልሃለሁ" አለው:: አጠመቀው:: በዚህ ምክንያት ይሔው እስከ ዛሬም "#መጥምቀ_መለኮት" ሲባል ይኖራል:: ቅዱስ ዮሐንስ በመጨረሻ ሔሮድስን ገሰጸው:: ንጉሡም ተቀይሞ ለ7 ቀናት አሠረው::

¤በዚህች ቀንም ልደቱን ባከበረ ጊዜ ወለተ ሔሮድያዳ በዘፈን አጥምዳ አስማለችው:: እርሱም የታላቁን ነቢይ ራስ አስቆርጦ በወጪት አድርጐ ሰጣት:: አበው "እምሔሶ ለሔሮድስ ይብላዕ መሐላሁ - ሔሮድስ መሐላውን በበላ በተሻለው ነበር" ይላሉ:: የቅዱስ ዮሐንስ ራሱ በርራ ስትሔድ አካሉን ግን ደቀ መዛሙርቱ ቀብረውታል:: (ማቴ. 3:1, ማር. 6:14, ሉቃ. 3:1, ዮሐ. 1:6)

¤ርጉም ሔሮድስ አንገቱን ካስቆረጠው በሁዋላ የመጥምቁ ቅዱስ ዮሐንስ ራሱ የጸጋ ክንፍ ተሰጥቷት ጌታችን ወዳለበት #ደብረ_ዘይት ሔዳ በፊቱ ሰገደች:: #ቅዱሳን_ሐዋርያት በአዩት ነገር ተገርመው ራሱን እጅ ነሷት::

¤ከዚሕ በሁዋላ ጌታችን #ኢየሱስ_ክርስቶስ ለቅዱስ ዮሐንስ ራስ የማስተማር ስልጣን ሰጥቶ አሰናበታት:: በመላው ዓለም ለ15 ዓመታት ስትሰብክ ኑራ በዚህች ቀን ዓረቢያ ውስጥ ዓርፋለች::

<<¤ አስማተ-ዮሐንስ መጥምቅ (የመጥምቁ ዮሐንስ ስሞች) ¤>>
1.ነቢይ
2.ሐዋርያ
3.ሰማዕት
4.ጻድቅ
5.ካሕን
6.ባሕታዊ/ገዳማዊ
7.መጥምቀ መለኮት
8.ጸያሔ ፍኖት (መንገድ ጠራጊ)
9.ድንግል
10.ተንከተም (የብሉይና የሐዲስ መገናኛ ድልድይ)
11.ቃለ አዋዲ (አዋጅ ነጋሪ)
12.መምሕር ወመገሥጽ
13.ዘየዐቢ እምኩሉ (ከሁሉ የሚበልጥ)

=>ጌታችን #መድኃኔ_ዓለም የመጥምቁ ዮሐንስን ምትረት አስቦ ይቅር ይበለን:: ጸጋውን: በረከቱንና ክብሩንም ያሳድርብን::
#ወስብሐት_ለእግዚአብሔር
https://t.me/yeberhanljoche